የተሳሳተ መረጃና የጥላቻ ንግግር የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ፈተና ናቸው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የተሳሳተ መረጃና የጥላቻ ንግግር የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ፈተና ናቸው ተባለ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2013(ኢዜአ) የተሳሳተ መረጃና የጥላቻ ንግግር የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ፈተና በመሆናቸው ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ተባለ።
የአለም ፕሬስ ነፃነት ቀን መረጃ ለህዝብ ጥቅም በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።
በዓሉ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፣በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ፣ዩኔስኮና አጋር አካላት ትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
በዚሁ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተወካይ ዶክተር ሄኖክ ስዩም ባለፉት ሶስት አመታት የመገናኛ ብዙሃንን ነፃነት ለማረጋገጥና ምህዳሩን ለማስፋት የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጠቅሰው በዚህም በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
የተደረጉት ማሻሻያዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸውና ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም በማረጋገጥ፤ አሁን ላይ መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ህዝብን የሚጠቅሙ እንጂ የሚጎዱ መሆን እንደሌለባቸው የገለጹት ዶክተር ሄኖክ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት አመታት በሚዲያው ዘርፍ በርካታ ማሻሻያዎች ቢደረጉም አሁንም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮች አሉ ብለዋል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን ዙሪያ የወጡ ህጎችን አለማክበር፣ ሚዛናዊነት የጎደላቸው መረጃዎችን ማቅረብ፣የአገርን ብሄራዊ ጥቅም ከሚያስጠብቁ መረጃዎች ይልቅ ብሄርን ከብሄርና ፣ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ መረጃዎች በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እነዚህን ተግዳሮቶች ለማለፍ መገናኛ ብዙሃንና የሚመለከታቸው አካላት በኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሰብሳቢ ወይዘሮ ትዕግስት ይልማ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች ከፍርሃትና ከስጋት ነጻ ሆነው የሚሰሩበት ከባቢ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
ይህንን እውን ለማድረግ መንግስት የጀመራቸውን ማሻሻያዎች በማጠናከር ለመገናኛ ብዙሃን ነፃነት መረጋገጥ አበክሮ ሊሰራ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ተወካይ ዩኪሚቶ ኖዞኬሲ ባለፉት ሶስት አመታት በሚዲያው ዘርፍ የተከናወኑት ማሻሻያዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ዩኔስኮም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በቀጣይም እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
በአገሪቱ የተሳሳቱ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ፈተና በመሆናቸው በዚህ ረገድ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል፡፡