ትውልዱ የአገሩን ዳር ድንበር አስጠብቆና እርስ በርስ ተስማምቶ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አለበት-- አንጋፋ አርበኛ - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ የአገሩን ዳር ድንበር አስጠብቆና እርስ በርስ ተስማምቶ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አለበት-- አንጋፋ አርበኛ

ሚያዚያ 25/2013 (ኢዜአ) ትውልዱ የአገሩን ዳር ድንበር አስጠብቆ፤ እርስ በርስ ተስማምቶ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አለበት ሲሉ አንጋፋው አርበኛ ግራዝማች አበበ ወርቅነህ ተናገሩ።
በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር አገው ምድር አውራጃ አንካሻ ወረዳ በጎመርታ ቀበሌ አሰም ስላሴ በተባለው መንደር የተወለዱት ግራዝማች አበበ ወርቅነህ የ100 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ አርበኛ ናቸው።
አባታቸው ከግራዝማች ወርቅነህ ብሩ በንጉስ ተክለሃይማኖት አገር ማቅናት ዘመቻዎች በዕውቁ የጦር አበጋዝ ራስ ደርሶ ጠቦ ስር ሆነው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከእንቦቦ እስከ ሰገሌ ዘመቻዎች ተሳትፈዋል።
በታላቁ የአድዋ ጦርነት ደግሞ በራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ጦር ስር በአድዋ ተራሮች በጀግንነት ጠላትን ተዋግተዋል።
ከአድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ የመጣውን የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራም እድሜያቸው ቢገፋም ከታናናሽ ወንድሞቻቸው ፊታውራሪ ደስታ ብሩና ቀኛዝማች በላይነህ ብሩ በትውልድ መንደራቸው ጠላትን ፊት ለፊት ተፋልመው የሕይወት መስዋትነት ከፍለዋል።
የአባታቸው የአርበኝነት ወኔ የወረሱት ግራዝማች አበበ ወርቅነህ ገና በአፍላነት እድሜያቸው ወደ አርበኝነት ተቀላቅለው ለአገራቸው ነፃነት በዱር በገደሉ ኳትነዋል።
በጎጃም አርበኝነትን ገና ጠላት ከመግባቱ አሀዱ ብለው የጀመሩት ገረመው ወንዳውክና ከበደ አለማየሁ የተባሉ ጀግኖች እንደሆኑ የሚገልጹት ግራዝማች አበበ፣ ደጋ ዳሞትን የአርበኝነት አስኳል ያደርጉታል።
እንደ ግራዝማች አበበ ትረካም ሆነ በአካባቢው በተደረጉ ጥናቶች አርበኞች ለመጀመሪያ ጊዜ በፋሺስት ኢጣሊያ ጠላት ጦር ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት በማድረስ ድል የተቀዳጁት ህዝቡ ደጃዝማች ማተቤ በሚል ማዕረግ በሚጠራው በልጅ ገረመው ወንዳውክ መሪነት በሰከላ፣ ይልማና ዴንሳ፣ ቋሪትና ሜጫ ወረዳዎች አዋሳኝ በምትገኘው ይዞራ በተሰኘችው ስፍራ ላይ በተደረገው የይዞራ ጦር ሜዳ ውሎ ነው።
በዚህ የተበሳጨው ጠላትም በ1929 ዓ.ም ወርሃ ነሃሴ በሁሉም አቅጣጫ ጦር በማሰባሰብ ወደ ይዞራ በማቅናት ላይ እያለ በነግራዝማች አበበ መንደር ጎመርታና በሰከላ ግሽ አባይ ላይ አርበኞች ከየአቅጣጫው ተጠራርተው ድል አድርገው መልሰውታል።
የግራዝማች አበባ አባት በወደቁበት የጎመርታው ጦር ሜዳም አርበኞች 16 መድፍና ሁለት ሺህ ጠመንጃ መማረካቸውን፤ የተገደለው ሃማሴን የሚባለው የኢጣሊያን ሰራዊት ለቀብር እስኪታክት መደምሰሱንና ነጭ ኢጣሊያን መማረኩን ይናገራሉ።
በጠላት ወረራ ዘመን አብዛኛው የጎጃም ጠቅላይ ግዛት በአርበኞች ቁጥጥር ስር ስለነበር ጠላትን ከምሽጉ ብቻ እንዲታጠር መደረጉን፣ ባንዳውም በአርበኞች ብርቱ ቅጣት መሰናዘር አለመቻሉን ያነሳሉ።
ይህ የተጠናከረ የአርበኝነት እንቅስቃሴም በአገረ እንግሊዝ ስደት ላይ የነበሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በሱዳን ካርቱም አድርገው በጎጃም በኩል በቀላሉ እንዲገቡ ማስቻሉን አውስተዋል።
የጠቅላላ አርበኞች የበላይ መሪዎችም በአገው ምድር እስከ ቋራ መተማ በመለስ ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ በዳሞት ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ፣ በሞጣ አውራጃና አካባቢው ልዑል ራስ ሃይሉ በለው፣ እንዲሁም ከደጀን እስከ ቢቸና አካባቢዎች ደጃች በላይ ዘለቀ እንደነበሩ ይተርካሉ።
ምንኩስናን የተቀበሉት የዛሬው የ100 ዓመታት የዕድሜ ባለጸጋ ግራዝማች አባ አበበ ወርቅነህ እድሜያቸው ቢገፋም፣ የአገር ፍቅር ወያኔያቸው አልነጠፈም፤ የአርበኞችን የጀግነነት መገለጫ የሆነውን የፉከራ ግጥም ድርደራም አልዘነጉም፤ አርበኞችንም አልዘነጉም።
በነቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ ስር የነበሩት ግራዝማች አበበም በጎመርታ፣ ይዞራ፣ ፋግታ፣ ዳንግላ፣ ግሽ አባይ፣ ኳኩራና ሌሎች ጦር ሜዳዎች ውለዋል።
ቀዳሜ አጼ ኃይለስላሴን ከስደት ሲመለሱ በመተከል ጉባ ወረዳ በር በማስከፈት ንጉሱን ከተቀበለው የዳሞት ጦር ጋር በመጓዝ ከኦሜድላ እስከ ደጀን እየተዋጉ ንጉሱን ወደ አዲስ አበባ ሸኝተዋል።
በአርበኝነታቸውም በንጉሠ ነገሥቱ እጅ የጦር መሳሪያ ስለመሸለማቸው፣ በኋላም በርካታ የወርቅና ብር ሜዳሊያዎች እንደተበረከተላቸው ገልጸዋል።
ከጎልተ ገዥ ቤተሰብ የሚወለዱት ግራዝማች አበበ ከነጻነት በኋላም ከ50 አለቃ ማዕረግ ጀምሮ እስከ ግራዝማችነት በወረዳ ሰላምና ጸጥታ ሃላፊነቶች አገልግለዋል።
በ1960 ዓ.ም በፈነዳው የጎጃም ገበሬዎች አመጽ ወቅትም በቋሪት ወረዳ ጣሊያ ልጃምበራ የተቀሰቀሰውን አመጽ ጦር መርተው አረጋግተዋል።
እኒህ ታላቅ ባለታሪክ ሰው ታዲያ ዛሬም ተወልደው ባደጉበት፣ ተድረው ተኩለው በወለዱበት በርስታቸው ጎመርታ በተሰኘችው የገጠር ሰፈር ምንኩስናን ተቀብለው ይኖራሉ።
በዘመናችን ጠላትን ለማባረር ራስ በራሳችን የጎበዝ አለቃ በመመራረጥ አገራችን ከጠላት ለማላቀቅ ለፍተናል የሚሉት ግራዝማች አበበ፣ ጠላትን በካምፕ ብቻ እንዲታጠር አድርገናል፤ ባንዳዎችንም አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት አሸንፈናቸዋል ይላሉ።
በአርበኝነት ዘመን የደሃ ገንዘብ የሚበላ አርበኛም በሚመራው ጎበዝ አለቃ የዛሬው ወጣት ትውልድ ኢትዮጵያን ጠባቂ፣ እምነቱና ምግባር ሰባቂ፣ እውቀት ሰናቂ በመሆን ኢትዮጵያ እንድትለመልም፣ ህዝቡ ከስደት እንዲገታ፣ ፋብሪካ እንዲስፋፋ በየደረጃውና በየሙያ ተስማምቶ መስራት አለበት ብለዋል።
ቀደምት አርበኞች ወራሪ ጠላት ሲመጣ በመተባበር አገራቸውን መጠበቃቸውን ገልጸው፤ የአሁኑ ትውልዱ በመተባበር የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጠብቆ ለመጨው ትውልድ ማውረስ እንዳለበት አሳስበዋል።
በቀድሞ አባቶች ዘንድ ኢትዮጵያዊያን በአገር ጉዳይ በዘርና ብሔር መከፋፋለ እንዳልነበራቸው ገልጸው፤ ከታሪክ የወረሷትን ጠብቀው ለዛሬው ትውልድ ማስረከባቸውን ያነሳሉ።
ዛሬም ምድረ ቀደምቷ አገር ከነታሪኳ ተጠብቃ እንድትኖር ሁሉም በየሙያው በጊዜው የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት ይገባዋል ብለዋል።
እርስ በርስ በሰላምና በመተሳሰብ መኖር፣ የአገር ሕልውና ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።