የኢትዮጵያን ጠላቶችን ለማሸነፍ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሊቆሙ ይገባል-- ልጅ ዳንኤል ጆቴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ጠላቶችን ለማሸነፍ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሊቆሙ ይገባል-- ልጅ ዳንኤል ጆቴ
ሚያዚያ 25/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ጠላቶች ለማሸነፍ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሊቆሙ ይገባል ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተናገሩ።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሚያዝያ 27 ቀን የሚከበረውን 80ኛ ዓመት የድል በዓል አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በጋራ ሊቆሙ ይገባል፤ ያሉንን የውስጥ ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው አገራችንን ለማሻገር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ትውልዱ ለአገር አንድነት የተከፈለውን መስዕዋትነት በመረዳት አሁንም አገር ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች አገሪቱን በዘርና በኃይማኖት ሊከፋፍሏትና ህዝቡና መሪዎች እንዳይተማመኑ ሴራ እያሴሩ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከ80 ዓመት በፊት ከገጠማት የውጪ ወረራ የሚመሳሰል ችግር እየገጠማት ነው በማለትም፤ ይህን በመቻቻልና በመከባበር ማለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
"ኃያላን መንግስታት ሳይቀሩ ከግፈኞችና ከአገር ጠላቶች ጎን ሲሆኑ የአገር ውስጥ ባንዳዎችም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሴራው ደጋፊ ሲሆኑ ይታያል ከዚህም መቆጠብ አለባቸው" ሲሉም ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም ጠላቶቿ ቢተባበሩባትም ሊያቆስሏት ይችሉ ይሆናል እንጅ አያሸንፏትም" ነው ያሉት ልጅ ዳንኤል።
የድል በዓል እንደ የአድዋ ድል በዓል በሁሉም አካባቢ አንዲከበርና እንዲታወቅ ብሎም ለትውልድ እንዲተላለፍ መንግስት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ በድል አድራጊነት ለህዝቦቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብና በቅኝ አገዛዝ ስር ለነበሩ ሁሉ ተስፋና ኩራት ሆና ቀጥላለች" ሲሉም ተናግረዋል።
በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአርበኞችን ታሪክ በማሰባሰብ ገድላቸው እንዲጻፍና ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመግለጫው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ-አሜሪካ ሲቪል ካውንስል የዘመቻና ሚዲያ ዳይሬክተር አቶ ስዩም ኃብተወልድ እንዳሉት የአሁኑ ትውልድ የበለጠ የአርበኝነት ስራ ይጠብቀዋል።
የዓባይ ግድብ እንዲጠናቀቅ፤በኢትዮጵያ ያሉትን ወቅታዊ ሁኔታዎች ለማለፍና አገሪቱን ለትውልድ ለማስተላለፍ የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለዋል።