ከ34 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ከአገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
ከ34 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ከአገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ ሃምሌ 25/2010 ከ34 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ከአገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት ገንዘቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ከሀምሌ 18 እስከ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከአገር ሊወጣ ሲል ነው። በዚህም መሰረት በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል ብቻ በህገ ወጥ መልኩ ከአገር ሊወጣ የነበረ 30 ሺህ 100 የአሜሪካን ዶላር 700 ዩሮ 4ሺ ድርሀም እና 27 ሺህ የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል። በተመሳሳይም ከሀምሌ 20 እስከ 23/2010 ድረስ በቶጎ ጫሌ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 2 ሺህ 137 የአሜሪካን ዶላር በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኤሌክትሮኒክስ፣ የአልባሳት እና ሌሎች እቃዎች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሲሞከር በቁጥጥር ስር መዋሉንም አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከአገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉ አይዘነጋም።