የብልጽግና ፓርቲ በአጋሮ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ፓርቲ በአጋሮ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ አካሄደ
ሚያዚያ 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲን መምረጥ የሃገር ልማትና አንድነትን ማስቀጠል ነው ሲሉ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በአጋሮ ከተማ ዛሬ ባደረጉት ሰልፍ ገለጹ።
በቅስቀሳ ዘመቻው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የፓርቲያቸውን ምስል የያዙ ቲሸርቶችን በመልበስ የተለያዩ መልዕክቶችን በማሰማት የቅስቀሳ ዘመቻ አካሄደዋል።
“ዶክተር አብይን መምረጥ ሀገርን ለተሻለ እድገት ማዘጋጀት ነው”፣ “ብልጽግናን እንመርጠዋለን፣ ዶክተር አብይን እንወደዋለን”፣ “ብልጽግናን መምረጥ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል መወሰን ነው”፣ “ብልጽግና ሰላም ፣ልማትና ዴሞክራሲን መምረጥ ነው” የሚሉና ሌሎችንም መፈከሮች አሰምተዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የአጋሮ ከተማ አመራር አቶ ነሲብ ያሲን እንዳሉት “የአጋሮ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይን መምረጥ በመቻላችን እንደ እድል እንቆጥረዋለን” ብለዋል፡፡
አክለውም “ብልጽግናን መምረጥ የኢትዮጵያን ትንሳኤ መምረጥ ማለት ነው ፣በመሆኑም ብልጽግናን በመምረጥ ለውጡን ወደፊት ማራመድ አለብን” ብለዋል፡፡
“የብልጽግና ጽህፈት ቤት የአጋሮ ከተማ ሀላፊ አቶ ነዚፍ መሀመድ አሚን በበኩላቸው ብልጽግና ለኢትዮጵያ አንድነት የሚታገል፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች የገረሰሰና ሰላምና ልማትን ለማፋጠን የሚተጋ ፓርቲ በመሆኑ ሊመረጥ ይገባል” ብለዋል፡፡
ብልጽግናን ምረጡ! ምልክታችን አምፖል ነው! ለህብረተሰባችን የለውጥ ብርሀን እናበራለን! ብለዋል አቶ ነዚፍ፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ የአጋሮ ከተማን ወክለው እንደሚወዳደሩ መገለጹ ይታወሳል፡፡