ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እድገትና ምርታማነት አሰሪና ሰራተኞች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

ሚያዝያ 23/2013 (ኢዜአ) አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23/2013 (ኢዜአ) ለኢንዱስትሪ እድገትና ምርታማነት የሰላም መስፈን የማይተካ ሚና ስላለው አሰሪዎችና ሰራተኞች የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ እለቱን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፤ ሰላም የተረጋጋ የኢንዱስትሪ እድገት እንዲኖርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ለማስቻል አንዱና ወሳኙ ነገር ነው።

ህብረተሰቡ ሰርቶ የሚገባውና የልፋቱን አግኝቶ የሚኖረውም ሰላም ሲኖር በመሆኑ አሰሪዎችም ሆኑ ሰራተኞች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው መስራት አለባቸው ብለዋል።

የሰራተኛው መብት፣ ጥቅም፣ የስራ ቦታ ደህንነትና ጤንነትን በአገሪቱ ህግ መሰረት በአብዛኛው የግል ድርጅቶች በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተከበረ አይደለም ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሰሪዎች ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የሰራተኞችን መብት፣ ጥቅምና የስራ ላይ ደህንነት አክብረው እንዲንቀሳቀሱ     ሰራተኞችም የኮሮናቫይረስን እየተከላከሉ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰራተኛው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በመጪው አገራዊ ምርጫም በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ታደለ ይመር በበኩላቸው ኮንፌዴሬሽኑ ሰራተኞች ተደራጅተው መብታቸውን እንዲያስከብሩ እና ምርትና ምርታማነት እንዲያሳድግ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ነገር ግን ጥቂት የማይባሉ አሰሪዎች ሰራተኞች እንዳይደራጁ እየከለከሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም አሰሪዎች የሰራተኞችን መብት በማክበር ለኢንዱስትሪ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ፤ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠርና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲረጋገጥ ከተለያዩ ባላድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰራተኛው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች የከተማ አስተዳደሩ በሂደት ምላሽ እየሰጠበት ይገኛል ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ጃንጥራር አባይ ናቸው።

ያለ ሰራተኛው ጉልህ ተሳትፎ እድገት የማይታሰብ በመሆኑ ድጋፋችሁ ተጠናክሮ ይቀጥል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሰራተኞች መጪው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አደራ እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን በየዓመቱ ሚያዝያ 23 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን እለቱ የዓለም የሰራተኞች ቀን ወይም ሜይ ዴይ እየተባለ ይጠራል። 

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1889 ማርክሲስት ኢንተርናሽናል ኮንግረንስ ሰራተኞች በቀን ከ8 ሰዓት በላይ እንዲሰሩ እንዳይገደዱ መደንገጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ቀደም ሲል አንድ ሰራተኛ በቀን ለ15 ሰዓታት እንዲሰራ በማስገደድ የጉልበት ብዝበዛ ሲደረግ ቆይቶ እ.ኤ.አ. በ1886 ሰራተኞች ተሰብስበው በተቃውሞ ሰልፉ በማካሄድ ለመብታቸው ትግል ጀመሩ።

ይህንኑ ተከትሎ ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን በየዓመቱ ሚያዚያ 23 ቀን የሚከበር ሲሆን የተለያዩ መሪ ሃሳቦችን በመቅረፅ ሰራተኞችን የሚመለከቱ የተለያዩ መልእክቶች ይተላለፉበታል።

ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን ዘንድሮ በዓለም 132ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ "የኮረናቫይረስን እየተከላከልን፣ በመደራጀት ለሰላምና ለምርታማነት እንሰራለን" በሚል ሃሳብ ተክብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም