ምክር ቤቱ ሕወሓት እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሃሳብ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ሕወሓት እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሃሳብ አሳለፈ
ሚያዝያ 23/2013(ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሃሳብ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ “የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ውይይት ማካሄዱን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ እና የመብት መከበር ጥያቄዎች እና ትግል አማካኝነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ መቆየታቸው ይታወሳል።
በዚህም የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል።
እነኚህ ጥቃቶች ኅብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋት እና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርጓል ነው ያለው።
እንደ መግለጫው እነዚህ ሁሉ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈጸሙ የነበሩ መሆኑን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።
ጥቃቶቹ ከጀርባቸው የፖለቲካ አስተሳሰብን መነሻ በማድረግ እና የፖለቲካ ዓላማን ወይም ግብን ለማሳካት በማሰብ በንጹሐን ዜጎች እና በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው።
የምክር ቤቱ መግለጫ እንደሚያስረዳው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የቆዩት ጥቃቶች የተለያዩ ፈጻሚ አካላት ነበሯቸው።
ከጥቃቶቹ ጀርባ ግን በዕቅድ፤ በገንዘብ፣ በሐሳብ እና በሰው ኃይል ሥልጠና በመደገፍ፤ የሚዲያ ሽፋን እና እገዛ በመስጠት ረገድ የመሪነት ሚናውን ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖች አሉ።
ኢትዮጵያን የማመሰቃቀል፤ የማዳከም እና የማፍረስ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች እነዚህን ቡድኖች በቅጥረኝነት እየተጠቀሙባቸው እንደሆነም ግልጽ ነው ብሏል።
“ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የቆዩዋቸው የጥፋት ተግባራት የሽብር ወንጀል ተግባራት መሆናቸውን ገልጿል።
እነዚህ ተግባራት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 ሥር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ ለሙሉ የሚያሟሉ ተግባራት እንደሆኑ በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል ብሏል።
እነዚህን የሽብር ተግባራት የፈጸሙ ድርጅቶች አባላትና እና ደጋፊዎቻቸውን እንደ ግለሰብ በተናጠል በሽብር ወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቶቹን የሽብርተኛ ድርጅት አድርጎ በመሰየም በሕጉ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይችላል ይላል መግለጫው።
ስለዚህ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና 19 መሠረት “ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የሥራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጭ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል ነው ያለው።
እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 23 መሠረት በተመሳሳይ ተግባር በተሰማሩ እና በዚህ ውሳኔ ሐሳብ መሠረት ከተሰየሙት የሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ትብብር፤ ትሥሥር ወይም የሐሳብ እና የተግባር ዝምድና ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም ይህ የውሳኔ ሐሳብ ተፈጻሚ ይሆናል ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።