ቀጥታ፡

ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍጹም ፍቅር የሰው ልጆችም እርስ በርሳቸው በመዋደድ እንዲያሳዩ ተጠየቀ

ሚያዚያ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍጹም ፍቅር ምዕመናን እርስ በርሳቸው በመዋደድ ፍቅርንና መልካምነትን እንዲያሳዩ ተጠየቀ።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የስቅለት በአል በሃይማኖታዊ ስርአት ዛሬ ተከብሯል።

በዕለተ አርብ የሚከበረው የስቅለት በአል ክርስቶስ ለሰው ልጆች ብሎ የከፈለውን መስዋትነት በማሰብ የእምነቱ ተከታዮች በስግደትና በጸሎት እንደሚያከብሩት የሃይማኖቱ አስተምሮ ያስረዳል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ መላከ ህይወት ቆሞስ አባ ወልደኢየሱስ ሰይፉ እለቱ የሚከበርበትን ሃይማኖታዊ ይዘት አስረድተዋል።

እለቱ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የክርስቶስ ጥንተ ስቅለት የሚታሰብበትና ክርስቶስ ለሰው ልጆች ብሎ መከራን የተቀበለበት እንደሆነ አስረድተዋል።

"ፈጣሪ የሰውን ልጅ ያለ ዋጋ የወደደበት፣ መከራን የተቀበለበት የፍቅር ጥግ የታየበት እለት ነው" ሲሉም ሃይማኖታዊ ይዘቱን አብራርተዋል።

በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍጹም ፍቅር ምዕመናን እርስ በርሳቸው በመዋደድ ፍቅርንና መልካምነትን እንዲያሳዩ መክረዋል።ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ካጠናከሩ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ችግሮች እንደሚያልፉም ገልጸዋል።

የእምነቱ ተከታዮችም እራሱን ለሰጣቸው አምላክ ታማኝ በመሆን በሰው ልጆች ዘንድ እየደረሰ ያለው ሞትና መፈናቀል እንዲቆም በፀሎትም በተግባርም እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በተለያየ ቦታ የተፈናቀሉ፣ ለችግር የተዳረጉና ረዳት የሌላቸውን ሰዎች ሁሉ በማካፈል ምዕመኑ ትንሳኤውን እንዲያከብርም ጠይቀዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምዕመናንም "እርስ በርስ መዋደድንና ፍቅር ከቤተሰብ በመጀመር አንድነትን ማጠናከር ያስፈልጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ቡጹዕ አቡነ ማቲያስ "ፈጣሪ የምዕመናንን ጸሎት ተቀብሎ ለኢትዮጵያ ሰላምና እንድነትን ያምጣ" ብለዋል።

የዕምነቱ ተከታዮች የትንሳኤን በአል ሲያከብሩ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በመተባበርና በመተጋገዝ መሆን እንደሚገባውም መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም