በአጣዬና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ኮማንድ ፖስቱ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በአጣዬና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ኮማንድ ፖስቱ ገለፀ
ሚያዚያ 22 /2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች በነበረው የፀጥታ ችግር በወንጀሉ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን በመለየት ለፍርድ እንደሚያቀርብ በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ፤ የፀጥታ ሃይሉ በአካባቢው የነበረውን የፀጥታ ችግር ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በነበረው ችግር ተዘግቶ የነበረውን መንገድ በማስከፈት የተቋረጡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ሥራዎች እንዲጀመሩ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስና በወንጀሉ መጠየቅ ያለባቸውን አካላት በመለየት በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሌተናል ጄኔራል ደስታ ተናግረዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ "በአካባቢው መረጋጋት በመፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎቶችና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ጀምረዋል" ብለዋል።
የስልክ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩንም ሌተናል ጄኔራል ደስታ ጨምረው ተናግረዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአካባቢው ማህበረሰብም አጥፊዎችን የማጋለጥና መረጃ የመስጠት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
"በችግሩ ላይ የአገር ውስጥና የውጭ አካላት፣ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና በመንግስት መዋቅር ስር ያሉ አንዳንድ አመራሮችም እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል" ያሉት ሌተናል ጄኔራል ደስታ፤ በማስረጃ የተደገፉ መረጃዎች የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ለችግሩ መንስኤ እና ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ገልጸው፤ ተሳታፊዎችን ኮማንድ ፖስቱ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ ማስረጃ አደራጅቶ ህግ ፊት እንደሚያቀርባቸው አረጋግጠዋል።
በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ግዳጅ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የልዩ ዘመቻ 3ተኛ አየር ወለድ ብርጌድ ሻለቃ አመራር በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት መኖሩን ተናግረዋል።
በአጣዬ ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችና አምስት ከተሞች ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ የሚታወስ ነው።