ቀጥታ፡

ማህበረሰቡ በእርድ ወቅት ለቆዳና ሌጦ ጥራት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደረግ ተጠየቀ

ሀዋሳ ፤ሚያዚያ 22/2013 (ኢዜአ) ለበዓል በሚኖረው የእርድ ስነ- ስርዓት ወቅት ማህበረሰቡ ለቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደረግ የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጠየቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ባጢሳ ዌዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፡ ህብረተሰቡ ለበዓሉ  በሚያከናውነው እርድ ለቆዳና ሌጦ ጥራት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለበት።

ሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው  ምርቶች ውስጥ አንዱ ቆዳና ሌጦ  በመሆኑ  በዕርድ ወቅት ቆዳ በስለት ሳይወጋና ሳይቀደድ በፍጥነት ለሚረከቡ ነጋዴዎች በማድረስ እንዳይበላሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በአቀማመጥ ምክንያት ለብልሽት እንዳይዳረግ ጨው በተገቢው መንገድ በመነስነስ አልያም ዘርግቶ አየር እንዲያገኝ መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በዚህ መልኩ በማዘጋጀት በወጣለት ዋጋ ተመን መሠረት በጊዜ ሰብሳቢዎች ጋር በማቅረብ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል 

በሲዳማ ክልል ሀዋሳን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ቆዳን በአግባቡ ሰብስቦ ወደ ማዕከል የሚያጓጉዙ ከ45 ነጋዴዎች ተለይተው ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

ለገበያ የሚቀርበው ቆዳና ሌጦ እንደ ጥራቱ ተለይቶ የበሬ ከ200 እስከ  300 ብር  የበግ  ከ60 እስከ 75 ዋጋ የወጣላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም