ቀጥታ፡

ጋዜጠኞች በምርጫ ወቀት ህዝብን ወደ ግጭት ከሚያመራ ዘገባ ሊቆጠቡ እንደሚገባ ተጠቆመ

አምቦ፣ ሚያዚያ 22 /2013 (ኢዜአ) 6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰለማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጋዜጠኞች ህዝቡን ወደ ግጭት ከሚያመራ ዘገባ መቆጠብ እንዳለባቸው ተጠቆመ ።

አምቦ ከተማ ለሶስት ቀን በግጭት ጥንቁቅነት ላይ ለጋዜጠኞች የተሰጠ ስልጠና ትናንት ተጠናቋል፡፡

የዘንድሮው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ፍትሃዊና ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል እድል ሊሰጡ  እንደሚገባ በመድረኩ  ተመላክቷል፡፡

የሰላምና ልማት ማእከል ከዩ.ኤስ.ኤይድ በመተባበር ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተወጣጡ ባለሙያዎች ስልጠናውን ሰጥቷል። 

ስልጠናው በምርጫ አዘጋገብ ዙሪያ ባለሙያዎች መከተል ስለሚገባቸው ሥነ ምግባር በማሳወቅ አቅምን ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በሰላምና ልማት ማእከል የሰላም ግንባታ ባለሞያና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ካሳሁን አብደታ ለኢዜአ እንደገለጹት የስልጠናው አላማ ጋዜጠኞች ከግጭት ነጻ የሆነና ሀሰተኛ መረጃዎችን ባለማሰራጨት እውነተኛነቱ የተረጋገጠ ዜና በመዘገብ ሞያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡

መገናኛ ብዙሀን በምርጫ ወቅት ለተለያዩ ተፎካካሪ ፓሪቲዎችም ሆነ ለመንግስት አካል የሚደርሱ መረጃዎችን በተሰጣቸው ሰዓት በእኩልና ታማኝነት እንዲያገለግሉ ስልጠናው አቅም የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።

ጋዜጠኞች በምርጫ ወቅት  ህዝቡን ወደ ግጭት ከሚያመራ ዘገባ መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል ፡፡

"የትኛውም ጋዜጠኛ የህዝቡን ስነልቦናና የአካባቢውን አኗኗር ዘይቤ በመረዳት ህዝቡን ወደ ግጭት ከሚያመራ  ዘገባ  በመቆጠብ ይጠቅማሉ ያላቸውን ጉዳዮች ብቻ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡

ጋዜጠኞች ሞያውንና የሞያውን ስነ-ምግባር ብቻ ያማከለ  ዘገባ ሊያቀርቡ እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የኦቢኤን ጋዜጠኛ ኃይለገብርኤል ጉደታ በሰጠው አስተያየት "ባለፉት አምስት ምርጫዎች ሲካሄዱ ጋዜጠኞው ራሱን ችሎ በሞያው እንዲመራና እንዲዘግብ የተደረገ አልነበረም" ብሏል።

"በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋዜጠኛው ራሱን ችሎ በስ-ነስርአት እንዲመራና በሞያው  እንዲዘግብ ለማስቻል የተዘጋጀው ስልጠና  ለምርጣው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊነት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል" ብሏል፡፡

የኢቢሲ ጋዜጠኛ ሲሳይ ሶሬሳ በበኩሉ "የትኛውንም አለመግባባቶችን በጥሬ ከመዘገብ ይልቅ ከተለያዩ አቅጣጫዎች መመልከት አለብን" ብሏል።

"የምንሰራለት ህዝብ እውነተኛ መረጃ ይፈልጋል" ያለው ጋዜጠኛው አንድን የፖለቲካ ፓርቲ አስበልጦ ሌላውን ማሳነስ ሳይሆን ሁሉንም ተወዳዳሪዎች በእኩል ማየት አለብን " ሲል ተናግሯል።

ለሶስት ቀን በቆየው ሰልጠና  ጋዜጠኞች ብጥብጥንና ግጭትን እንዴት ይረዳሉ፤ ጋዜጠኝነትና ግጭት የሚያገናኛቸው ምንድ ነው ፤በሚሉና በሌሎችም የግጭት ሁኔታዎች ላይ በባለሞያዎች የግንዛቤ ትምህርቶች ተሰጥተዋል፡፡


በስልጠናው ላይ የኢዜአ፣ ኢቢሲ፣ ኦቢኤን፣ ፋና ብሮድካስትና የፕሬስ የተውጣጡ ጋዜጠኞችና የኮሚኒኬሽን ባለሞዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም