የትንሳኤ በአል ገበያ የበሬ እና በግ ግብይት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የትንሳኤ በአል ገበያ የበሬ እና በግ ግብይት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች ተናገሩ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2013/ኢዜአ/ የትንሳኤ በአል ገበያ የበሬ እና በግ ግብይት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች ተናገሩ፡፡
በትንሳኤ በአል ገበያ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ቅናሽ ቢታይም የእርድ ሰንጋዎች እንዲሁም የበግና ፍየል ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን ሸማቾች ተናግረዋል፡፡
የኢዜአ ሪፖርተር በመዲናዋ የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የበአል ግብይት ምን እንደሚመስል ምልከታ አድርጋለች፡፡
በዚህም መካከለኛ የሚባለው በግ ከ2 ሺህ 500 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ሲሆን ትልቁ ደግሞ ከ7 ሺህ እስከ 8 ሺህ ብር ይሸጣል።
አነስተኛ በሬ 38 ሺህ ብር እንዲሁም ትልቁ ደግሞ 48 ሺህ ብር ለሽያጭ ሲጠራ የተስተዋለ ሲሆን ዶሮ ከ400 አስከ 600 ብር በመሸጥ ላይ ነው፡፡
የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ከፍተኛ አቅርቦት በመኖሩ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ ማሳየቱን ሸማቾች ተናግረዋል።
በእለቱ ገበያ ቀይ ሽንኩርት ከ10 ብር ጀምሮ፤ ነጭ ሽንኩርት 80 ብር፣ ቲማቲም 16 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ቀደም ካሉት ጊዜያት በተለየ የቀይና ነጭ ሽንኩርት ዋጋ ብር ቅናሽ ቢያሳይም በእርድ እንስሳት ላይ ከፍተኛ ዋጋ ታይቷል።
የአትክልትና ፍራፍሬ ሲትገበያይ ያገኘናት ወጣት ሂላሪ ጌታሁን በአትክልት ላይ ቅናሽ መኖሩን ገልፃልናለች፡፡
የበግና ፍየል ገበያ ከሌሎቹ የበአል ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር ጭማሬው የተጋነነ ባይባልም ለውጥ መኖሩን በግብይት ላይ ያገኘነው አቶ ዘሪሁን ወልዴ ነግሮናል።
ሆኖም የእርድ ሰንጋ በብዛት የገባ ቢሆንም የዘንድሮው ዋጋ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡
የዶሮ ግብይትም የዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ከ550 ብር እስከ 950 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ሸማቾች ነግረውናል።
አቶ ስጦታው አመነ እንዳሉት የዶሮ ገበያ አምና 350 ብር እና 400 ብር የነበረው አሁን ግን 900 እና 950 እየተባለ ነው፤ በጣም ውድ ነው።
አጠቃላይ የዘንድሮ የበአል ገበያ በእርድ ከብቶች እና በዶሮ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡