ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ሁለት ክፍለ ከተሞች በሕገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ መድሃኒት ተገኘ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2013 በአዲስ አበባ ሁለት ክፍለ ከተሞች በሕገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ መድሃኒት በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ፤ ባለፈው አንድ ወር ከፌዴራል ፖሊስና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በመዲናዋ በሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር ላይ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በመዲናዋ ሁለት ክፍለ ከተሞች በተደረገ ፍተሻም በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የነበረ መድሃኒት በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።

በተደረገው ጥናት ሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውር አለባቸው የተባሉ ስድስት ቦታዎች መለየታቸውን አስታውሰው በአራቱ ላይ ፍተሻ ተካሂዷል ነው ያሉት።

በዚህም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 "ፓስተር አደባባይ" አካባቢ እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት "አራት መንታ" እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ብዛት ያላቸው መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ተከማችተው መያዛቸውን ጠቁመዋል።

በህገ ወጥ መልኩ ተከማችቶ የተገኘው መዲሃኒት በአዲስ ከተማ በግለሰብ በመኖሪያ ቤት ውስጥ እንዲሁም በየካ ክፍለ ከተማ ደግሞ በአንድ መድኃኒት አከፋፋይ ድርጅት የጥበቃ ቤት ውስጥ ነው።

መድኃኒቱንና የህክምና ግብአቶቹን አከማችተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ከተያዙት መድኃኒቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡና በጥንቃቄ ተከማችተው መከፋፈል ያለባቸው እንዲሁም በጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ብቻ የሚታዘዙ እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።

ለህጻናትና ለእናቶች የሚሰጡ መድኃኒቶችና ከመንግስት የጤና ተቋማት የተሰረቁ የሳንባ ነቀርሳና የኤች አይቪ ኤድስ መመርመሪያ ኪቶችም መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የተገኙት መድኃኒቶች በዋጋ ቢተመኑ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ መሆናቸውንም ነው ወይዘሪት ሄራን ያስረዱት።

በቅርብ ጊዜ የተያዙት መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአቶች በአጠቃላይ የሚያወጡት ወጪና ብዛታቸው ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

ሕብረተሰቡ የጤና ግብአቶች ሕጋዊ ፈቃድ ካላቸው ተቋማት ብቻ መግዛት እንዳለበትና በህክምና ባለሙያ መታዘዝ ያለበትን  ከባለሙያ ትዕዛዝ ውጭ መጠቀም እንደሌለበትም ገልጸዋል።

ሕብረተሰቡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ በ84 82 የነጻ የስልክ መስመር ማሳወቅ እንደሚችልም ነው ዋና ዳይሬክተሯ የጠቆሙት።

በክትትልና ቁጥጥር ሥራው ለተሳተፉ የጉምሩክ ኮሚሽንና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ረዳት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ እንዳለው፤ የተያዙት መድኃኒቶችና የሕክምና ግብአቶች ጥቅም ላይ ቢውሉ በሕብረተሰቡ ላይ የጤና ጉዳት ያስከትሉ ነበር ብለዋል።

ሕገ-ወጥ የጤና ግብአቶች ዝውውርን የመከላከሉ ሥራ በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የፀረ-ኮንትሮባንድ ቁጥጥርና ክትትል ዲቪዥን አባል ረዳት ኢንስፔክተር አሊ ሰይድ በተቀናጀ መልኩ የተከናወነው የኦፕሬሽን ሥራ ውጤታማና በጥብቅ ክትትል የተመራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በሕገ-ወጥ የጤና ግብአቶች ዝውውር ሰንሰለቱን በማጥናት ከምንጩ የማድረቅ ሥራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም