መከላከያ ሚኒስቴር በአጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች የ2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሚኒስቴር በአጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች የ2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
ሚያዚያ 22 / 2013 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በአጣየ እና በከሚሴ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀንኣ ያደታ ለአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ አስረክበዋል።
ዶክተር ቀንኣ በዚህን ጊዜ እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሰረዊት ከህዝብ አብራክ የወጣና ያለ ዘውግ ልዩነት ህዝብን እኩል እያገለገለ የሚገኝ ኃይል ነው።
ድጋፉም ሰራዊቱ ለህዝብ ያለውን አለኝታነት አመላካች መሆኑን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አከባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ መደፍረሶች ባለፈው ስርዓት በተዘራው ጥላቻና ልዩነት ምክንያት የሚፈጠሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ይህን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ የኢትዮጵያ ውጭና የውስጥ ጥላቶች ግንባር ፈጥረው ሀገር ለማተራመስ እየሰሩ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች ደግሞ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሆኖም የሀገር መከላከ ሰራዊት ከሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ኅብረተሰቡ ችግሩ እንዲፈታ ከሀገር መከላከያ ጎን በመሆን እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራና ኦሮሞ ህዝቦችንም ሆነ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ የሚደረገው ሙከራ "የማይሳካ ከንቱ ድካም" ነው ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ጀግንነቱ የተመሰከረለትና ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን ገልጸዋል።
ባላፉት ሶስት አስርት ዓመታት ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦችን ለማለያየት ከፍተኛ የጥላቻ ትርክትና ዘር መዘራቱን ነው የተናገሩት።
ይህም በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ እያስከተለ ከፍተኛ መስዋትነት እንድንከፍል እያደረገን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል በመሆን በርካታ አፍሪካዊያን በነጻነት እንዲኖሩ አብነት መሆኗን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ዜጎች ነጻነታቸውና ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው ተገፎ እንዲኖሩ መፍቀድ የለብንም ብለዋል።
በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠር ችግር የኔ ነው በማለት የአንዳችንን ህመም ሌሎቻችን መጋራት አለብን ነው ያሉት።
የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍም በአማራ ክልል ህዝቦች ስም ምስጋና አቅርበዋል።