ቀጥታ፡

ደቡብ ሱዳንን ከመደገፍ አኳያ ኢትዮጵያ በዘመናት የመንግስታት መቀያየር ያልተለወጠ የፀና አቋም አላት--አምባሳደር ነቢል ማህዲ

ሚያዚያ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳንን ከመደገፍ አኳያ በዘመናት የመንግስታት መቀያየር ያልተለወጠ የፀና አቋም ያላትና አሁንም በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ ከማድረግ አንፃር የቀጠለ መሆኑን አምባሳደር ነቢል ማህዲ አስታወቁ።

በደቡብ ሱዳን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንትና የአገሪቱ የመሰረተ ልማት ክላስተር ሰብሳቢ ታባን ደንግ ጋር መክረዋል።

አምባሳደር ነቢል ደቡብ ሱዳንን ከመደገፍ አኳያ ኢትዮጵያ በዘመናት የመንግስታት መቀያየር ያልተለወጠ የፀና አቋም እንዳለ ጠቅሰው፣ አሁንም በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም ሀገራቱ በመሰረተ ልማትና በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ ከማድረግ አንፃር የቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል።

በትግራይ ከተከናወነው የህግ ማስከበር እርምጃ በኃላ መንግስት 70 በመቶ የሚሆነውን የሰብዓ እርዳታ በመሸፈን እያቀረበ መሆኑን አብራርተውላቸዋል። የህዳሴ ግድብን በተመለከተ 65 ሚሊዮን በላይ የአገሪቱ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳስ ግድብ ለኃይል ማመንጨት ተግባር የሚውል ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።

አያይዘውም ግብፅና ሱዳን የኢትዮጵያን የናይል ውሃ የመጠቀም ልዑላዊ መብት ማከበር እንዳለባቸው አሳስበዋል። አምባሳደር ነቢል ኢትዮጵያ የታችኞቹን ተፋሰሱ አገራት የመጉዳት አጀንዳ የሌላት መሆኑን ገልፀው፣ በሁሉም አገራት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ እንዲደረስ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል።

አክለውም ግድቡ ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አንስተው፣ የመጀመሪያው ዙር የግድቡ መሊት ሱዳንን ከአስከፊ የጎርፍ አደጋ የታደጋት ስለመሆን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ታባን ደንግ በበኩላቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ ትስስር አውስተው፣ ኢትዮጵያ በቀጠናው ካላት ወሳኝ ሚና አንፃር የኢትዮጵያ ሰላም ለደቡብ ሱዳን ብሎም ለቀጠናው ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ አክለው በትግራይ ሰላም ለማስፈንና ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ረገድ በመንግስት የተከናወኑ ተግባራትን አድንቀው፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይን ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈፀሚያነት ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን አውግዘዋል።

አክለውም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታዳሽ የኃይል ምንጭነት ለአካባቢው ያለውን ጠቀሜታ ጠቅሰው፣ የናይል ወንዝ የሁሉም የተፋሰሱ አገራት የተፈጥሮ ሰጦታ በመሆኑ በአግባቡ ከተጠቀሙበት ለሁሉም በቂ እንደሆነ ተናግረዋል።ምክትል ፕሬዝዳንቱ የአካባቢው አገራትን በመንገድ መሰረተ ልማት የማስተሳሰር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር )

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም