ቀጥታ፡

በጾም ወቅት የተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማገዝ የአብሮነት፣ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን ማሳደግ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) 21/2013 በጾም ወቅት የተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማገዝ የአብሮነት፣ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶና የእስልምና እምነት ተከታይ ምዕመናን በጾም ወቅት ላይ ይገኛሉ።

ይህን የጾም ወቅት ታሳቢ በማድረግም በጎ አድራጊዎች አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣በመደገፍና በማገዝ ላይ ትኩረት አድርገው ይንቀሳቀሳሉ።

ድጋፍ ከሚያደርጉት መካከልም የ‘'እኔ እያለሁ ወገኔ አይራብም'’ ቡድን ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ 10 ሺህ ያህል አረጋዊያንና ችግረኛ ወገኖች የሶስት ወር አስቤዛ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ቡድኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ወሎ ለሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ የቡድኑ አስተባባሪ ወጣት ዲኑ ዓሊ ለኢዜአ አስታውቋል፡፡

ወጣቶቹ ከምግብ ፍጆታ ጀምሮ አልባሳትና የሴት ልጅ ንፅህና መጠበቂያ ቁሶችን‘ቅድሚያ ለሰብዓዊነት’ በሚል መርህ በሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኩል በማሰባሰብ ላይ ናቸው።

የባይሽ ኮልፌ የመረዳጃ ማህበርም የጾምና የበዓላት ወቅትን በመጠቀም ለአዛውንቶች፣ ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናትና ለችግረኛ ወገኖች የሚውል ድጋፍ ለማሰባሰብ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

የተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማገዝና መደገፍ ከምንጊዜውም በላይ በዚህ የጾም ወቅት ተገቢ መሆኑን የምትገልጸው የድጋፍ አሰባሳቢ ቡድኑ አስተባባሪ ቴምር ሐሰን፣ አቅም ያለው ለታረዙ፣ ለተጠሙና ለተራቡ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ አለበት ትላለች።

በዚህ የጾም ወቅት አንዱ ለአንዱ በመተጋገዝና በመረዳዳት ማሳለፍ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን የጠቆሙት የበጎፈቃድ ስራ ላይ የተሰማሩት አስተባባሪዎች፤ የመደጋገፍ ባህል በመመለስ በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የቆየ የአብሮነት፣የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን በማስቀጠል በኩል ወጣቶች  ኃላፊነት አለብን የሚሉትአስተባባሪዎች፣ ሁሉም በየአካባቢው ድጋፍ እንዲያሰባስብ ጠይቀዋል።

ዜጎች ተባብረው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን እንዲደግፉ ጥሪያቸውንም አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም