ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳዔ በዓልን ሲያከበር ከኮሮና ወረርሽኝ እራሱን በመከላከል ሊሆን ይገባል -ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳዔ በዓልን ሲያከበር ከኮሮና ወረርሽኝ እራሱን በመከላከል ሊሆን ይገባል -ኢንስቲትዩቱ
ሐዋሳ ሚያዚያ 21/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትና የመያዝ ምጣኔ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ህዝበ ክርስቲዩኑ የትንሳዔ በዓልን ሲያከብር መዘናጋትን በማስቀረት ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት አሳሰበ።
የሃይማኖት መሪዎችና ምዕመናን በበኩላቸው ከወረርሽኙ ስርጭት እራስን ለመከላከል የእምነቱ ተከታዮች የዘንድሮን የፋሲካ በዓል በየቤቱ ሆኖ በጥንቃቄ ሊያከብር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር ማቴ መንገሻ ለኢዜአ እንደገለጹት ለዓለም ፈተና ሆኖ የዘለቀው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአከባቢው ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
በክልሉ የኮሮና ምልክት ባላቸው ሰዎች ላይ በጤና ተቋማት በተደረገ ምርመራ እስከ ጥር ወር ድረስ 13 በመቶ የነበረው በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ በመጋቢትና በሚያዚያ ወር 2013 ከ46 እስከ 54 በመቶ ማሻቀቡን ገልጸዋል።
"ምልክት ሳያሳዩ በየቤታቸው ተጠቅተው የሚሞቱ ዜጎች በርካቶች ናቸው" ያሉት ሃላፊው የተለያዩ አገልግሎቶች መስጠት የሚገባቸው የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጫና ውስጥ መውደቃቸውን አውስተዋል።
"በቫይረሱ ተጠቅተው ወደ ጽኑ ህክምና የሚገቡ ቁጥራቸው እየተበራከተ በመምጣቱ ኦክሲጅንና አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ እጥረት ጋር ተዳምሮ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል" ብለዋል።
እስከአሁን ከተመረመሩ ከ63 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ውሰጥ 8 ሺህ 160 በላይ በቫይረሱ መያዛቸውንና ከመካከለቻውም 158 ቱ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አስታውቀዋል።
አሁን ላይ በታይፈስና ታይፎይድ ተይዘው ለህክምና የሚመጡ ሰዎች ምርመራ ሲደረግላቸው ኮሮኖ ሆኖ እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።
የቫይረሱን ተጽዕኖ ለመቋቋም ጥንቃቄ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ገልጸው ካልተመረመረ በስተቀር ማን ላይ ቫይረሱ እንዳለ ስለማይታወቅና የመዛመት እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ህዝበ ክርስቲያኑ የዘንድሮውን የትንሳዔ በዓል ሲያከብር ጥንቃቄ በተሞላበት እንዲሆን ዶክተር ማቴ አሳስበዋል።
በቫይረሱ ምክንያት ቤተክርስቲያኗ በርካታ አገልጋዮችና አባላት አጥታለች ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የማዕከላዊ ደቡብ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ቄስ ኢያሱ ጠግቾ ናቸው።
አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭትና እያስከተለ ያለው ሞትና ጉዳት ከፍ እያለ በመምጣቱ አስፈላጊ ጭንቃቄ ማድረገ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
"በተለይ በዓላት በምናከብርበት ወቅት የተለመደው መሰባሰብ ቀርቶ ምዕመኑ በየቤቱ ማክበር እንዳለበት ያሳሰቡት ቄስ ኢያሱ ከጤና ሚኒስተርና ከመንግስት የሚሰጡ ምክሮች መተግበር ይገባል" ብለዋል።
በሽታው እየከፋ ሲመጣ እየታየ ያለው ቸልተኝነትና መዘናጋት ተገቢ ባለመሆኑ ሶኖዶሱ በስሩ የሚገኙ ሰበካዎችና ማህበረ ምዕመናናት ግንዛቤ የማሳደግ ስራ መጀመሩን ገልጸው ምዕመኑ የጥንቃቄ መልዕክቶች እንዲተገብሩ አሳስበዋል።
በዓሉ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በመስቀል በመሞት ያሳየው ፍቅር መገለጫ በመሆኑ ህዝበ ምዕመኑ የተቸገሩትን ማሰብና ለሃገርና ለህዝብ ወደ ፈጣሪ መለመን እንዳለበት መልዕእክት አስተላልፈዋል።
የደቡብ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ጌቱ አያሌው በበኩላቸው
በኮሮና ምክንያት በርካቶችን እያጣን ስለሆነ የዘንድሮን የትንሳዔ በዓል ህዝበ ክርስቲያኑ ከመሰባሰብ ይልቅ በየቤቱ ሆኖ ማክበር እንደሚገባው አሳስበዋል።
ህዝበ ክርስቲያኑ ይህ ክፉ ጊዜ አልፎ የእፎይታ ጊዜ እንዲመጣ ከጤና አካላት የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶች በመተግበር በጸሎት እንዲተጋ ጠይቀዋል።
አብያተ ክርስቲያናትም ርቀትን በመጠበቅ የአምልኮ ስነ ስርዓት እንዲካሄድ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።