የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ለአገር ሰላም ሰራተኞች የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ለአገር ሰላም ሰራተኞች የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሚያዝያ 21/2013 የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የሀገርን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሠራተኛው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓለም አቀፉን የሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ) አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በእዚሁ ወቅት ሠራተኞች ሰርተው ለመኖርና ወጥተው ለመግባት እንዲችሉ ሰላም ዋነኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰላም የሰፈነበት አገር የተረጋጋ ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር በማድረግ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እንደሚያግዝም አብራርተዋል።
"በመሆኑም የአገር ሰላም እንዲጠበቅ መላው ሠራተኛ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰላም ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ኮንፌዴሬሽኑ በሰላም ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦችን በጋራ የመኖር እሴት እየሸረሸሩ እንደሚገኙም ጨምረው ገልጸዋል።
ህዝቦች ሰላማቸው እንዲጠበቅ፣ ተከባብረው እንዲኖሩና የማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሕይወት እንዳይጠፋ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
ለእዚህም የሚፈጠሩ ግጭቶችን በኃላፊነትና በሰከነ ውይይት በመፍታት ለሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባ ነው አቶ ካሳሁን ያስረዱት።
የሰራተኞችን የሙያ ደህንነት ማስጠበቅ ለሀገር ኢኮኖሚ ፋይዳው ጉልህ መሆኑንም አብራርተዋል።
በመሆኑም በሥራ ቦታ የሙያ ደህንነትና ጤንነትን ለማስጠበቅ የወጡ ህጎች ተግባራዊ እንዲሆኑም አቶ ካሳሁን አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸው አንዳንድ የግል ድርጅቶች ተቀጥረው ይሰሩ ለነበሩ ሠራተኞች ችግራቸው ታይቶ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይዋቃል።
የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ) “ የኮሮና ወረርሽኝን እየተከላከልን፤ በመደራጀት ለሰላምና ለምርታማነት እንሰራለን” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።