ቀጥታ፡

ለትግራይ ክልል የ371 ሚሊዮን ብር መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ተሰራጨ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሚያዝያ 21/2013 በትግራይ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በ371 ሚሊዮን ብር መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶችን ማቅረቡን የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ገለጸ።

የኤጀንሲው ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል የመድሃኒት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ከፍተኛ ትኩረት ተደርጓል።

በክልሉ የጸጥታ ችግር ከተከሰተ በኋላ ከህዳር ወር ጀምሮ ቅርንጫፎች ሥራ መጀመራቸውን ተከትሎ የመድሃኒቶች አቅርቦት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።  

ኤጀንሲው ለክልሉ መድሃኒትና ቁሳቁሶችን ለማቅረብ በመቀሌና በሽሬ ካሉት ቅርንጫፎች በተጨማሪ የአጎራባች የጎንደርና የደሴ ቅርንጫፎችን መጠቀሙን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 371 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው መድኃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ለክልሉ መቅረቡን ገልጸዋል።

ከእነዚህም 181 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው መድሃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ለጤና ተቋማት መሠራጨታቸውን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።  

በቀጣይ ቀሪዎቹ መድሃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችም ከተከማቹበት ማዕከል ወደ ተለያዩ የጤና ተቋማት በቅርቡ እንደሚሰራጩ ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም የክልሉን ጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ጭምር ወደ ክልሉ መላኩን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

በሌላ በኩል ኤጀንሲው የኮሮናቫይረስ ክትባት ወደ አገር ከገባ በኋላ በጥንቃቄ ለማከማቸትና ለማዘዋወር ለወራት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ኤጀንሲው ባሉት ሁሉም ቅርንጫፎች ክትባቶቹን ለማስቀመጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ማቀዝቀዣዎች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም 17 ማቀዝቀዣዎች ለክትባቱ ሥርጭት ተዘጋጅተው መመደባቸውን ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን ወደ አገር ከገባው 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን አስትራ ዜኒካ ክትባት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ክትባት ከሶማሌ ክልል 5 ወረዳዎችና ከመተከል ዞን ውጭ በሁሉም የአገሪቱ አከባቢዎች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።

ከቻይና የገባው 300 ሺህ የሲኖ ፋርም ክትባትም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ለከተማ አውቶብስ አሽከርካሪዎች እንዲውል እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።  

ኤጀንሲው ከዚህ በኋላ የሚመጡትን ክትባቶች በቀዝቃዛ ስፍራ የማስቀመጥ ሰንሰለትን ተጠቅሞ በማከማቸት ለማከፋፈል መዘጋጀቱን ዶክተር አብዱልቀድር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም