የዚምባብዌ ምርጫ ኮሚሽን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት እስከ ሐምሌ 28 እንደሚያሳወቅ ገለጸ

67
አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010 የዚምባቡዌ ምርጫ ኮሚሽን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን እስከ ሐምሌ 28 እንደሚያሳወቅ ገለጸ። ዚምባቡዌ ከትናንት በስቲያ የፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምክር ቤት ምርጫ ማካሄዷ የሚታወስ ሲሆን ከአራት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ድምጽ ሰጥቷል። በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ላይ 23 እጩዎች ተወዳድረዋል። የዚምባቡዌ ምርጫ ኮሚሽን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምጽ ቆጠራ እየተካሄደ መሆኑንና ውጤቱን እስከ ፊታችን ቅዳሜ እንደሚያሳውቅ መግለጹን የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎት አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጿል። የምርጫው ውጤት በኮሚሽኑ እስኪገለጽ ድረስ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው የተወዳደሩ እጩዎችና እጩዎቹን የወከሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪዎቻችን እየመሩ ነው አሸንፈዋል በማለት እያወጡት ያለው መረጃ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል። በዚምባቡዌ የምርጫ ህግ መሰረት በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አንድ እጩ 51 በመቶ ድምጽ ካላገኘ ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንደሚካሄድ ያስቀምጣል። በዚሁ መሰረት በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው አንድም እጩ 51 በመቶ ድምጽ ካላገኘ ቀጣይ ምርጫ ነሐሴ 8 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚካሄድ የምርጫ ኮሚሽኑ ያወጣው መርሃ ግብር ያሳያል። በፕሬዚደንታዊው ምርጫ  የህብረት እና የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ (ኤምዲሲ) ፓርቲ ወክለው የተወዳደሩት ኔልሰን ቻሚሳ አሸንፈዋል በሚል ፓርቲያቸው በመግለጽ ላይ ይገኛል። የቀድሞውን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ የተኩት የ75 ዓመቱ ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና የህብረት እና የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ (ኤምዲሲ) ፓርቲ እጩና ጠበቃ ኔልሰን ቻሚሳ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ዋንኛ ተፎካካሪዎች ናቸው። በተያያዘ የዚምባቡዌ ምርጫ ኮሚሽን የፓርላማ ምክር ቤት ምርጫ ውጤትን ዛሬ ይፋ ያደረገ ሲሆን የገዢው የዛኑ ፔኤፍ ፓርቲ 109 መቀመጫ በማግኘት አብላጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፉን አስታውቋል። የህብረት እና የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ንቅናቄ (ኤምዲዲሲ) ፓርቲ 41 መቀመጫ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። የዚምባቡዌ የፓርላማ ምክር ቤት 210 መቀመጫዎች ያሉት ነው። የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድንና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በቅርብ ቀናት ውስጥ በዚምባቡዌ ምርጫ ዙሪያ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም