በከተማዋ የስቅለትና ትንሳኤ በዓላት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን በመተግባር እንዲከበሩ ዝግጅት ተደርጓል -ቤተክርስተያኗ - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የስቅለትና ትንሳኤ በዓላት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን በመተግባር እንዲከበሩ ዝግጅት ተደርጓል -ቤተክርስተያኗ
ሀዋሳ ሚያዝያ 20/2013 (ኢዜአ ) በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት የስቅለትና ትንሳኤ በዓላት የኮሮና መከላከያ መንገዶችን በመተግበር እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርሲቲያን አስታወቀች ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳዎች ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ላዕከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ባንቡራ ለኢዜአ እንደገለፁት ቤተክርስቲያኗ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ሀገር ከገባ ጀምሮ ለምእመኖቿ አስፈላጊውን የጥንቃቄ መልዕክ ስታስተላልፍ ቆይታለች።
"የቤተክርስቲያኗ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተልዕኮ ህዝቡን ከነፍስና ከሥጋ ጉዳት መታደግ ነው" ያሉት ላዕከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት ጾምና ፀሎት በማወጅ ፈጣሪ ለሀገር ምህረትና ሠላምን እንዲያወርድ ምህላና ፀሎት ስታደርስ መቆየቷን ተናግረዋል።
በሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት የኮቪድ መከላከያ መንገዶች በአግባቡ እንዲተገብሩ የጋራ ጉባኤ በማዋቀር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመክተዋል።
የፊታችን አርብና እሁድ በቤተክርስቲያኗ በድምቀት በሚከበሩት የስቅለትና የትንሳኤ በዓላት በርካታ ምእመናን የሚታደሙበት በመሆኑ ሁሉም ሰው ርቀቱን በመጠበቅና ራሱን ከኮሮና በመከላከል እንዲያሳልፍ ለህዝበ ክርስትያኑ መመሪያ መተላለፉን አስታውቀዋል።
በሁሉም አጥቢያዎች የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በተደራጀና ቅንጅት ባለው መልኩ ኮሮናን የመከላከል ሥራ እንዲሰሩ፤ በዓላቱ በሚከበሩበት ዕለትም የማስተባበር ተግባሩን እንዲመሩ መደረጉን ጠቁመዋል።
"ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት የክርስቶስን የመስቀል ላይ ፍቅር በማሰብና ያለውን ለተቸገሩ በማካፈል ማሳለፍ ይገባዋል" ብለዋል።
በቤተክርስቲያኗ የሲዳማ ሀገረስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ምክትል ተቀዳሚ ሰብሳቢ ወጣት ታምራየሁ ግርማ በበኩሉ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ አስፈላጊ የመከላከያ ቁሳቁሶችን በማዘጋጀትና በማቅረብ እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድቷል።
ዐቢይ ፆም ከገባ ጀምሮ ተግባራቱን መቀጠላቸውን ገልፆ ለስቅለትና ለትንሳኤ በዓላት የተጠናከረ የጥንቃቄ ሥራ ለመስራት ኮሚቴዎችን በማዋቀር በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግሯል።
በከተማዋ በደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሰሞነ ሕማማት የሥግደት ሥርዐት ላይ ያገኘናቸው አቶ ታሪኩ አለማየሁ "በቅዳሴ ሥርዐት ወቅት ራሳችንን ከኮሮና ለመጠበቅ የሚያስችለንን ጥንቃቄ በማድረግ ነው" ብለዋል።
ምዕመኑ በቤተክርስቲያን ውስጥ ማድረግ ስላለበት ጥንቃቄ በቂ ግንዛቤ እንዳደበረ ተናግረዋል።
ወረርሽኙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በዓሉን በቤት ውስጥ በምናከብርበት ወቅትም እንደወትሮው መሰባሰብ ሳይበዛ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ብሎም የተቸገሩ ወገኖቻችንን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዘበዋል።