በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚስተዋለው ያልተቀናጀ አሰራር በሀገር ሃብት ላይ ኪሳራ እያስከተለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚስተዋለው ያልተቀናጀ አሰራር በሀገር ሃብት ላይ ኪሳራ እያስከተለ ነው
ሚያዚያ 20/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባልተቀናጀ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየደረሰ ያለው የሃብትና የጊዜ ኪሳራ እየተባባሰ መምጣቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
61 አገር አቀፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች በካሳ ክፍያና በጸጥታ ችግር ምክንያት መጓተታቸውም ተገልጿል።
የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በበኩሉ ''ጉዳዩ ከአቅሜ በላይ ነው'' ብሏል።
ይህ የተባለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ መሪነት የፌዴራልና የክልል የሥራ ሃላፊዎችና የመሰረተ ልማት ተቋማት ተወካዮች በተቀናጀ የመሰረተ ልማት አተገባበር ላይ ባደረጉት ውይይት ነው።
በመሰረተ ልማት ላይ የተሰማሩ ተቋማት ስራቸውን ተናበውና ተቀናጅተው ባለመስራታቸው የመንግስትና የህዝብ ሃብት እንዲባክን ከማድረግ ባለፈ ፕሮጀክቶቹ ጥራት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ በውይይቱ ተነስቷል።
አገራዊ የካሳ ክፍያ አዋጅ በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑና ለመንገድ ግንባታ ብቻ የሚወጣው የካሳ ክፍያ 10 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተገልጿል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የመንገድ ግንባታ ሊጀመር መሆኑን ሲሰሙ ህገ-ወጥ ቤቶችን በመገንባት ያልተገባ ካሳ የሚጠይቁ ግለሰቦች መኖራቸውም ተነስቷል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በኢትዮጰያ ባልተቀናጀ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰ ነው።
መንግሥት የመንገድ ፈንድን ጨምሮ በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡን አስታውሰው፣ ይሁንና ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች በመዘግየታቸው ከታሰበው በጀት በላይ እያስወጡ ነው ብለዋል።
በአሁን ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ 184 ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ያነሱት ኢንጂነር ሃብታሙ፣ ከነዚህ መካከል 61 ፕሮጀክቶች በካሳ ክፍያና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ተጓተዋል ብለዋል።
ይህም ለተጨማሪ ወጪና ጊዜ ከመዳረጉ ባለፈ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመስራት ማነቆ መሆኑን አብራርተዋል።
አንዳንድ የልማት ተነሺዎች የተጋነነ የካሳ ክፍያ መጠየቅ፣ ካሳ ከተከፈለ በኋላ ንብረታቸውን አለማንሳት፣ የተቋራጮች አቅም ማነስም ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት በምክንያትነት ተነስተዋል።
ከመንገድ መሰረተ ልማት ውጭ በኤሌክትሪክ፣ በውሃ፣ በቴሌኮምና በባቡር ፕሮጀክቶች ላይ ያለው የቅንጅት ክፍተትም ኪሳራ እያስከተለ መሆኑ ተነስቷል።
የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር በበኩላቸው የመሰረተ ልማት ተቋማት ተናበውና ተቀናጅተው አለመከወናቸው የመልካም አስተዳደር ችግር መፍጠራቸውንና ይህም የአገሪቷን ውስን ሃብት እያባከነ ነው ብለዋል።
ኤጀንሲው በ2006 ዓ.ም ቢቋቋምም ወደ ስራ የገባው በ2009 መሆኑን አስታውሰዋል።
ይሁንና የኤጀንሲው አደረጃጀት፣ የማስፈጸምና የመፈጸም አቅም ውስንነት የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ አድርጎታል ነው ያሉት።
ኤጀንሲው ከአስፈጻሚ ተቋማትና ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት የሰው ሃይልና ሎጀስቲክስን ጨምሮ ችግሮች እንዳሉበት ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሮ ሰዓዳ ገለጻ ፕሮጀክቶች ሲዘገዩ በየደረጃው ያሉ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስርዓት መዘርጋት አስካልተቻለ ድረስ ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የተሰማሩ ተቋማት ስራቸውን በጋራ ማቀድ፣ መገምገምና መፈጸም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተለይም በካሳ ክፍያና በጸጥታ ችግር ግንባታቸው የተንጓተቱትን 61 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ችግር ለመፍታት በየደረጃው የሚገኙ የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት መፍትሄ ማፈላለግ አለባቸው ብለዋል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላትም ፕሮጀክቶቹን በአካል ተገኝተው ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ አሳስበዋል።
በካሳ ክፍያ ላይ ሁሉም ክልሎች ወጥ የሆነ የሰራር ስርዓት መዘርጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል አፈ ጉባኤው።
ምክር ቤቱ በካሳ ክፍያም ሆነ በፕሮጀክቶች መዘግየት ተጠያቂነት ላይ ያሉ የህግ ክፍተቶችን ፈትሾ ማስተካከያ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።