ዩኒቨርሲቲው በቻይና መንግስት ድጋፍ ያስገነባውን የስልጠና ማዕከል አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በቻይና መንግስት ድጋፍ ያስገነባውን የስልጠና ማዕከል አስመረቀ
ሚያዚያ 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ከቻይና መንግስት ባገኘው ድጋፍ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን የስልጠና ማዕከል አስመረቀ።
የስልጠና ማዕከሉ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ እያደረገች ያለችውን ጥረት በመደገፍ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የተገነባው ሉባን የስልጠና ማዕከል ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ስራው በአንድ ዓመት መጠናቀቁ ተነግሯል።
በማዕከሉ የምረቃ ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ይህ ማዕከል ከስልጠና ባሻገር ለኢንዱስትሪ ባለሙያዎች የምርምር ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ተጠቁሟል።
አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን የማዕከሉ መገንባት ተማሪዎች ሙያዊ ችሎታዎችን በማዳበር የዘመናዊ ኢንዱስትሪ ልማት ስራን ለማጎልበት ለሚያደርጉት ጥረት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
የሉባ የስልጠና ማዕከል ኢትዮጵያ የ10 ዓመቱን የኢኮኖሚ ልማት ዕቅዷን በተሟላ ሁኔታ እንድታሳካ ከወዲሁ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና በቻይና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሙያ ስልጠና መስክ ያለው የልምድ ልውውጥና ትብብር የበለጠ እንደሚጠናከርም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት የአገራቱን የረጅም ዓመታት ጠንካራ ግንኙነት አስታውሰዋል።
ለምረቃ የበቃው የስልጠና ማዕከል አገራቱ በትምህርት ዘርፍ የሚያደርጉት ትብብር አንዱ ማሳያ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ቻይና በኢትዮጵያ የዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ግንባታና በስራ እድል ፈጠራ አይነተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኑንም አንስተዋል።
የሉባን ስልጠና ማዕከል የአገሪቷን የኢንዱስትሪ ልማት አጀንዳዎች ለማገዝ ወቅታዊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ እያደረገች ያለውን ጥረት በመደገፍም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ በረቻ በበኩላቸው ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ትብብሩ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የስልጠና ማዕከሉ መገንባት በሜካኒክስ፣ በሮቦቲክስ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች የመማር ማስተማር ሂደቱን ያሻሽለዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ማዕከሉ የተሻለ ክህሎትና ዕውቀት ከማስጨበጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ባለሙያዎች የሥልጠናና ምርምር ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ጠቁመዋል፡፡