ቀጥታ፡

የሙያ ደህንነትና ጤንነት አስተዳደር ወቅቱን በሚመጥን ልክ እያደገና እየሰፋ አይደለም - የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን

አዲስ አበባ ሚያዚያ 20/2013 (ኢዜአ) "የሙያ ደህንነትና ጤንነት አስተዳደራችን ወቅቱን በሚመጥን ልክ እያደገና እየሰፋ አይደለም" ሲሉ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ተናገሩ፡፡

የዓለም የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቀን "እናልም፣ እንዘጋጅ እና ለወረርሽኙ ምላሽ እንስጥ! ለቀውሱ ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ሥርዓት አሁኑኑ እንተግብር!" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ኮንፌዴሬሽን ዕለቱን አስመልክተው የሦስትዮሽ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።

ለኮቪድ-19 የሥራ ቦታ ምላሽ በመስጠት ረገድ ተከናወኑ ሥራዎች ላይም ተወያይተዋል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቀን የሥራ ቦታዎችን ከማንኛውም አደጋና የጤና ጉዳት ለመከላከል እንዲሁም በዚሁ ሳቢያ የሚከሰቱ የህይወትና የአካል ጉዳቶችና ጥፋቶችን ለመግታት የሚከበር ነው ብለዋል።

የሥራ ሁኔታዎችን ለማሻሻልና ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር የሚያስችሉ ስልቶችን ለመተግበር፣ የሠራተኛ ደህንነት ጥበቃ ባህልን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

በአዲስ መልክ የሚከሰቱ የጤና ጠንቆችን መንስኤ ለመረዳትና ለመከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ ስልቶች ለመንደፍና የአሠራር ዘዴዎችን በመሪ መልዕክት በማዘጋጀት እንዲተገበሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በሥራ ቦታ ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት እንደ ማህበረሰብ አባል ሠራተኞችን በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል።

ሠራተኞችን በሞት ማጣት፣ የህክምና ወጪ መናር፣ ከሥራ መቅረትና ምርታማነት መቀነስ የድርጅቶችና ሴክተሮችን ትርፋማነት እየተፈታተነው ይገኛል ነው ያሉት።

የወረርሽኙን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስና የሥራ ቦታን ምቹ ከማድረግ አኳያ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት፣ የአሰሪዎች ፌዴሬሽንና የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ተገቢ ምላሽ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በቅንጅት፣ በትብብርና በቁርጠኝነት ባለመሥራታችን የሙያ ደህንነትና ጤንነት አስተዳደራችን ወቅቱን በሚመጥን ልክ እያደገና እየሰፋ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ለሠራተኞች ከለላ ባለመስጠቱ፣ ደህንነቱና ጤንነቱ ያልተጠበቀ የሥራ ቦታ ለማስተካከል ውጤታማ የሆነ ሥራ ባለመስራቱ ምክንያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሥራው ዓለም ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩም ገልፀዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የዓለም የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቀን በዓለም ለ18ኛ በኢትዮጵያ ለ16ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም