የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከቶች ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 350 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማሰባሰቡን አሰታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከቶች ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 350 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማሰባሰቡን አሰታወቁ
መቀሌ ፤ ሚያዚያ 20/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከቶች በትግራይና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተፈጠረው ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 350 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ማሰባሰቡን አስታወቁ።
የአህጉረ ስብከቶቹ ልኡካን አባላት ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ጋር በሰብአዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋም ዙሪያ በመቀሌ ከተማ ተወያይተዋል።
የተሰበሰበው ገንዘብ ከዲስፖራው የተገኘ ድጋፍ መሆኑ ተመልክቷል።
ከልኡካኑ መካከል በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የካሊኒፎሪያ ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁእ አቡነ ቴዎፍሎስ ፤ በክልሉ በተፈጠረው ችግር ማዘናቸውን በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል።
ልኡካኑ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርሲቲያን አህጉረ ስብከቶች ወክሎ እንደመጣ የተናገሩት ብፁእ አቡነ ቴዎፍሎስ የተፈጠረው ችግር በአካል ለማየት በክልሉ እንደተገኙ ተናግረዋል።
በክልሉ በተፈጠረው ችግር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመርዳትና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻቸውን ለመወጣት ኮሚቴ አቋቁመው ዝግጅት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሃገረስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ሃላፊ ሊቀ ስዩማን ቄስስ ጥላሁን አበበ በበኩላቸው፤ አህጉረ ስብከቶች በትግራይና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተፈጠረው ችግር ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 350 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ከዲያስፖራው አሰባስበው ማምጣታቸውን አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው የአህጉረ ስብከቶቹ ሉኡካን አባላት በክልሉ በአካል ተገኝተው ድጋፍ ለማድረግ በመምጣታቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።
በክልሉ ሰላምና ልማት እንዲመጣ የሃይማኖት አባቶች ድጋፍ ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ሙሉ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ህዝቡን ለመቋቋም እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የልኡካን አባላቱ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ 12 ሃገረስብከት ወክለው እንደመጡ ተገልጿል።