ማህበራቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚገመት ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበራቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚገመት ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ
ደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ሚያዚያ 20/2013 (ኢዜአ) የተለያዩ ማህበራት በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ዞኖች ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብና አልባሳት ድጋፍ አደረጉ።
በአዲስ አበባ የአማራ ወጣቶች ማህበር ከሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች 500 ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብ እህልና አልባሳት በድጋፍ አስረክቧል።
ማህበሩ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ያደረገው ብርድልብስ፣ ፍራሽና አንሶላ እንዲሁም ዘይት፣ ፓስታና ማኮሮኒን ጨምሮ የተለያዩ የምግብና አልባሳት አይነቶችን ነው።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወጣት ዘነበ በለጠ ድጋፉን ባስረከበበት ወቅት እንደገለጸው ድጋፉ ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተሰበሰበ ነው።
ድጋፉ የተፈናቃዮችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቀነስ መደረጉን ጠቁሞ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ አኗኗራቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አመላክቷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንግዳሸት በጋሻው በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት በተፈጸመባቸው ጥቃት የተፈናቀሉ ወገኖች በአካባቢው ካለው ቀዝቃዛ አየር ንብረት ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ችግር ላይ ናቸው።
ወገኖቹ ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ በመገንዘብ ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ሌሎች ድርጅቶች፣ ማህበራትና ባለሃብቶችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በተመሳሳይ ሌሎች ማህበራትም በደቡብ ወሎ ዞን ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህልና አልባሳት ድጋፍ አድርገዋል ።
ድጋፉን ያደረጉት መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ የወሎ መረዳጃ ማህበራትና በረካ የተሰኘ በጎ አድራጊ ማህበር ነው።
ከተደረገው ድጋፍ መካከል 500 ኩንታል ዱቄት፣ 300 ፍራሽ፣ 471 ብርድ ልብስና ስድስት ጥቅል የፕላስቲክ ምንጣፍ እንደሚገኙበት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ አስታውቀዋል ።
ማህበራቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው የተፈናቃዮች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመሆኑ መንግስታዊና መንግሰታዊ ያልሆኑ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ።
የ"በረካ" በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማህበር ተወካይ አቶ ኡመር ብርቁና በአሜሪካ የሚገኙ የወሎ መረዳጃ ማህበር ተወካይ አቶ ተስፋዬ አሊ ድጋፉን ለዞኑ አስተዳደር አስረክበዋል ።
በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ16 ሺህ በላይ መድረሱን ከዞኑ አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያመላክታል ።