የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኘ
ሚያዚያ 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለፁ። የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ የገንዘብ መጠንም 698 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
የባንኩ የዘጠኝ ወራት እቅድ ክንውንና አፈጻጸም በዛሬው እለት የተገመገመ ሲሆን ባንኩ ካገኘው 55 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ የተጣራ ትርፍ መሆኑ ተገልጿል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለጹት ባንኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ102 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያገኘ ሲሆን አጠቃላይ የባንኩ የተቀማጭ የገንዘብ መጠንም 698 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ባንኩ በዘጠኝ ወራት የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ124 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዶ በ102 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በማሳደግ የእቅዱን 82 ነጥብ 4 በመቶ አሳክቷል ብለዋል።
በዚህም የባንኩ በአጠቃላይ የተቀማጭ የገንዘብ ክምችት የበጀት አመቱ ሲጀመር ከነበረው ብር 595 ነጥብ 5 ቢሊዮን ወደ 698 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ማደጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 216 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር፤ ከውጭ ሐዋላ ደግሞ 2 ነጥብ 13 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱም ተገልጿል፡፡
ባንኩ ከሰጣቸዉ የተለያዩ ብድሮች 36 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 54 ነጥብ 5 በመቶ አሳክቷል ብለዋል፡፡
የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት 62 አዳዲስ ቅርንጫፎችን መክፈቱንም ይፋ አድርገዋል።
በዚህም አጠቃላይ የባንኩን የቅርንጫፎች ቁጥር 1 ሺህ 666 ደርሷል።
አዲስ በተከፈቱት ቅርንጫፎች 885 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጸዋል።
በበጀት አመቱ 4 ነጥብ 27 ሚሊዮን አዳዲስ ሂሳቦች ተከፍተዉ አጠቃላይ የተቀማጭ ደንበኞች ሂሳብ ቁጥር 29 ነጥብ 37 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
የባንኩን አሰራር ለማዘመን የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመቅረጽ በመተግበር ላይ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡