ቀጥታ፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የስራ አካባቢና የሙያ ደህንነት ጠንቅ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20/2013(ኢዜአ)የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት ለሰራተኞች የስራ አካባቢና የሙያ ደህንነት ጠንቅ እየሆነ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በየአመቱ ሚያዚያ 28 ቀን የሚከበረውን ዓለም ዓቀፉን የሙያ ደህንነት ጤንነት ቀን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

ዓለም አቀፉ የሙያ ደህንነት ጤንነት ቀን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ19 ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ የሚከበር ይሆናል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ተክሌ ደሬሳ እንደገለጹት ፤ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት በስራ ላይ አደጋዎች እና ከስራ ጋር በተያያዘ በሚመጡ በሽታዎች ምክንያት ለከፍተኛ አእምሮአዊም ሆነ አካላዊ ጉዳት ይጋለጣሉ።

በዚህም በየትኛውም የሙያ መስክ ላይ ያሉ ሰራተኞች ሥራ ቦታ ላይ ለደህንነትና ለጤና ቅድሚያ መስጠትና ራሳቸውን መጠበቅ ይገባቸዋል።

ከሥራ ጋር ተያያዥነት ላላቸው አደጋዎች እና ህመሞች ብሎም ጉዳቶች ትኩረት በመስጠት ጤናማ የስራ አካባቢን መፍጠር ይገባልም ብለዋል።

በዚሁ ወቅት የሙያ ደህንነትና ጤንነት ማህበር ተወካይ አቶ ነጋ ኮቶ ሰራተኞች በየትኛውም አካባቢ ላይ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው ተጠብቆ መስራት አለባቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በስራ ቦታ ላይ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ እያሳደረ የሚገኝ ወቅታዊ ችግር መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሰራተኞች ደህንነታቸውና ጤንነታቸው ተጠብቆ በስራ ላይ ቢሰማሩ በአደጋ ምክንያት ከሚደርስባቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ተጽእኖ ራሳቸውን መከላከል እንደሚችሉም ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የሥራ ስምሪት በሽታ መከላከል ስርዓት ጉድለት በሰራተኞች እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ህብረተሰብ ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ አለው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት ስጋት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሰራተኞች፣ በስራዎቻቸው እና በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህንን አሳሳቢና ወቅታዊ ችግር ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል እና መቆጣጠር የሁሉም ግዴታ ነው ብለዋል።

ሰዎችን ለማዳን እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጤናማ የስራ አካባቢን ለመፍጠር አሳሳቢ ከሆነው ወረርሽኝ ራስንና ሌላውንም መጠበቅ ይገባልም ነው ያሉት።

የዓለም ጤና ደርጅት ያወጣው መመሪያ እንደሚያመለክተው የኮቪድ 19 መዛመትን ለመከላከል በስራ አካባቢዎች ሰራተኞች በተጠጋጋ መልኩ ስራ ማከናወን የለባቸውም።

የስራ አካባቢ በቂ አየር የሚተላለፍበት እንዲሆንና በተለያየ ጊዜ ፀረ ተህዋስ ኬሚካል መረጨት እንዳለበት ይመክራል።

ሰራተኞችም በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሃሳቦች መተግበር እንዲሁም የግል ንፅህናቸውን መጠበቅ ይጠበቅባቸዋል።

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሙያ ደህንነት ጤንነት ቀን "እናልም፣ እንዘጋጅ እና ለወረርሽኙ ቅድሚያ እንስጥ፤ ለቀውስ ምላሽ የሚሰጥ የሙያ ደህነትና ጤንነት አመራር ስርአት አሁኑኑ እንተግብር" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚከበረው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዓለም ላይ በየዓመቱ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰራተኞች በስራ ላይ አደጋዎችና ከስራ ጋር በተያያዘ በሚመጡ በሽታዎች ይጠቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም