ቀጥታ፡

አሮጌው የብር ኖት በመቀየሩ ምክንያት 126 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ ገብቷል...ብሔራዊ ባንክ

ሚያዚያ 19/2013 (ኢዜአ) አሮጌው የብር ኖት በመቀየሩ ምክንያት አዲስ የባንክ ሒሳቦች በመከፈታቸው 126 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ መግባቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ባንኩ የብር ኖት ቅየራው በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ ዛሬ የምስጋናና የእውቅና መርሃ ግብር አከናውኗል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ዋጋቸው ከ262 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ አዲስ የብር ኖቶች መታተማቸውን ገልፀው፤ ከዚህ ውስጥ 185 ቢሊዮን ብር ለባንኮች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

የስርጭት እና የገንዘብ ቅየራው ሂደት ውጤታማ በሆነ መልኩ መከናወኑንም ዶክተር ይናገር ገልጸዋል።

በገንዘብ ቅየራው ምክንያት ሁለት ሚሊዮን ዜጎች አዲስ የባንክ ሒሳብ መክፈታቸውን ተናግረው፤ በዚህም 126 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ መግባቱን አስታውቀዋል።

ከብር ኖት ቅየራ ጋር በተያያዘ የወጡ መመሪያዎች ለፋይናንስ ተደራሽነቱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ዶክተር ይናገር ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ቅየራው ህገ-ወጦችን በማዳከም ህግን ተከትለው ለሚሠሩ ዜጎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ለሁሉም የተመቸ ህጋዊ የግብይት ስርዓት ፈጥሯል።

"በትግራይ የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በክልሉ የብር ኖት ቅየራውን ሂደት አስተጓጉሎ የነበረ ቢሆንም በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል" ብለዋል።

ለሥራው መሳካት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ሌሎች ተቋማት የድርሻቸውን እንደተወጡ ተገልፆ እውቅናና ምስጋና ተበርክቶላቸዋል።

አዳዲሶቹ የብር ኖቶች ረዘም ላለ ጊዜ እንዲያገለግሉ ህብረተሰቡ በጥንቃቄ እንዲጠቀማቸው ዶክተር ይናገር ጥሪ አቅርበዋል።

በገንዘብ ቅያሬው የተለወጡ የብር መጠኖች ባለ 10፣ ባለ 50 እና ባለ 100 ብር ኖቶች ሲሆኑ ባለ 200 ብርም ለመጀመሪያ ጊዜ መታተሙ ይታወቃል።

ብሮቹን ለማሳተም መንግስት በአጠቃላይ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም