የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 24ኛ ማዕከሉን በሚዛን አማን ከተማ ከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 24ኛ ማዕከሉን በሚዛን አማን ከተማ ከፈተ
ሚዛን፣ ሚያዝያ 19/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 24ኛ ማዕከሉን በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ ተመርቆ ተከፈተ።
በምረቃው ስነስርዓት ወቅት እንደተገለጸው፤ ማዕከሉ ጥራት ያለውን የቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ዞን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ያሳድገዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ በወቅቱ እንዳሉት፤ ማዕከሉ የተከፈተበት የቤንች ሸኮ ዞን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የቡና ምርት ካላቸው አካባቢዎች አንዱና የተፈጥሮ ጫካ ቡና በስፋት የሚመረትበት ነው።
በምዕራብ ዞኖች በተፈጥሮ የጫካ ቡናና በቡና ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች በብዛት የሚገኙበት በመሆኑ ምርቱን ማዕከል ወዳለበት ስፍራ በማጓጓዝ የሚፈጅባቸውን ጊዜና እንግልት እንደሚያቃልል ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ በዞኖቹ የሚመረተውን ቡና በቀጥታ በመሸጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አመልክተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረውን ምላሽ እንዲያገኝ መንግስት ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው በክልሉ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ጥራት ያለውን የቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ዞን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብለዋል።
በስነስርዓቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትር ዴኤታ ምስጋናው አረጋን ጨምሮ ሌሎችም የፌደራልና የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።