በአውሮፓ በአምስት አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለልማት ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአውሮፓ በአምስት አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለልማት ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
ሚያዚያ 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) በ2013 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በአውሮፓ በአምስት አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለልማት ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ የተመራ ልዑካን ቡድን በጀርመንና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዳያስፖራ አገራዊ ተሳትፎና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትናንት የበይነ መረብ ውይይት አካሄዷል።
በውይይቱ ወቅት በ2013 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በበርሊንና ፍራንክፈርት በሚገኙ ኢትዮጵያ ሚሲዮኖች አስተባባሪነት በጀርመን፣ በቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ፣ ዩክሬንና ስሎቫኪያ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃው ያመለክታል።ድጋፉ የተሰበሰበው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል፣ ለገበታ ለአገር፣ለአገር መከላከያ ሰራዊትና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ባሉ ጉዳዮች እያደረገ ላው ገንቢ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ሀሰተኛ ትርክቶችን በማጋለጥ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እያከናወነ ያለው የማስረዳት ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና የዳያስፖራው ሚናን በሚመለከት የመወያያ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል።
የዳያስፖራ አባላትም በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያን ለማዳን ከመተባበር በስተቀር ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል።ኤጀንሲዉ በሚሰጣቸው የዳያስፖራ አገልግሎቶች፣ በአገራዊ ፕሮጀክቶች፣ በእውቀትና ክህሎት ሽግግር፣ በፐብሊክ ዲፕሎማሲና አድቮኬሲ ዘርፍ የዳያስፖራውን አስተዋፅኦ ስለማሳደግ እንዲሁም የጥምር ዜግነት የሚፈቀድበትን ሁኔታ በተመለከተ አስተያየቶችን አቅርበዋል።
በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ኢትዮጵያን ከእንግዲህ ወደኋላ የሚመልሳት ነገር የለም፤ መንግሥትና ሕዝብም በጋራ በመቆም አንድነታቸውን ጠብቀው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ይሻገራሉ ብለዋል።
ዳያስፖራውም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያከናወነ ያለውን አበረታች ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።በበርሊን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጀርመንን ጨምሮ ፖላንድ፣ ስሎቫኪያ፣ ቼክሪፐብሊክና ዩክሬን አገራትን ይሸፍናል።