አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የአዕምሯዊ ፈጠራ መብቶቻቸውን ማስጠበቅ ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የአዕምሯዊ ፈጠራ መብቶቻቸውን ማስጠበቅ ይጠበቅባቸዋል
አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የአዕምሯዊ ፈጠራ መብቶቻቸውን እንዲያስጠብቁ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አሳሰበ።
ጽህፈት ቤቱ ዓለም አቀፉን የአዕምሯዊ ንብረት ቀን ዛሬ አክብሯል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአዕምሯዊ ንብረት ቀን "አዕምሯዊ ንብረትና አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ሀሳባቸውን ያካፍሉ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው።
በመድረኩ የአዕምሯዊ ንብረትና አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ያላቸው ትስስር ላይ የሚያተኩር ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን የበዓሉ መከበር ዓላማ እንደተናገሩት የህዝቦችን የአዕምሯዊ ንብረት ግንዛቤ በማሳደግ ለአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ተገቢውን ዋጋ ለመስጠት ነው ብለዋል።
ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጀርባ ያለውን የፈጠራ ችሎታ በመገንዘብ አካባቢያዊ የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታትም እንዲሁ።
አብዛኛዎቹ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የአዕምሯዊ ንብረት ፈጠራ መብት እንዳላቸው አያውቁም ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም በተመሳሳይ ምርቶች የገበያ ድርሻቸውን እንዳያጡ የአዕምሯዊ ንብረት ውጤታቸውን በማስመዝገብ መብቶቻቸውን እንዲያስጠብቁ አስገንዝበዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
ምዝገባው ንግዳቸው በተወዳዳሪነት እንዲቀጥልና ስራቸውን ለማሻሻል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸወ በመጠቆም።
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ አምራቾችና የፈጠራ ባለቤቶችም የገንዘብ እጥረት ተግዳሮት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
አንዳንድ ፖሊሲዎችና ደንቦች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር በሰጡት ምላሽ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤቶች የተሰጣቸውን የባለቤትነት ማረጋገጫ በመያዝ ብድር የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።
በፖሊሲዎችና ደንቦች ላይ ክለሳ እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ጽህፈት ቤቱ በቴክኖሎጂ፣ በንግድ ምልክት፣ በቅጂ መብት የፈጠራ ስራዎቻቸውን ላስመዘገቡ ድርጅቶች የእውቅና የምስክር ወረቀት አበርክቷል።
ዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ቀን በዓለም ለ21ኛ በኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።