ቀጥታ፡

የውሃ ስፖርቶች ፕሬዚዳንቱ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተላለፈውን ውሳኔ አልቀበልም አሉ

ሚያዚያ 18/2013 የውሃ ስፖርቶች ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ተሾመ ሶርሳ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተላለፈባቸውን ውሳኔ እንደማይቀበሉት አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ሚያዚያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ተሾመ ሶርሳን ከሃላፊነታቸው ማንሳቱን አስታውቋል።

ጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔውን ያሳለፈው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፕሬዚዳንቱ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ ያስቀመጠውን ውሳኔ ተቀብሎ በማጽደቅ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ከኃላፊነታቸው የተነሱት "ውክልና ሳይሰጣቸው ባለፈው መጋቢት በተካሄደው የኦሊምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ላይ ተሳትፈዋል" በሚል ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

አቶ ተሾመ ሶርሳ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ስብሰባ መሳተፋቸው ትክክለኛና አግባብነት ያለው መሆኑን አስታውቀዋል።

በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው ከተሳተፉት ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና ዘጠኝ ክልሎች መካከል "አምስቱ በኃላፊነቴ እንድቀጥል ድምጽ ሰጥተውኛል" ሲሉም ነው የተናገሩት።

አራቱ በሚቀጥለው ጊዜ እስከሚካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያገለግሉ ድምጽ መስጠታቸውንና ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ድምጸ-ተዓቅቦ ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።

ነገር ግን በውሳኔው መሰረት በኃላፊነቴ መቀጠል ሲገባኝ ያለአግባብ ከኃላፊነት እንድነሳ ተወስኖብኛል ነው ያሉት።

መገናኛ ብዙሃን የፌዴሬሽኑን ጠቅላላ ጉባዔ ሽፋን እንዲሰጡ አለመጋበዛቸውን አስታውሰው፤ ይህም በጉባዔው የተነሳው ትክክለኛ ሃሳብ ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን በማሰብ ነው ብለዋል።

ውሳኔው በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ጫና እና በፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ግፊት መመወሰኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም "ውሳኔው አግባብነት የሌለው በመሆኑ አልቀበለውም" ብለዋል።

ችግሩ በሠላም መፈታት የማይችል ከሆነ ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ የውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን እንደሚሳውቁም ነው የገለጹት።

ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት የሚያደረጉ የውሃ ስፖርት አትሌቶች አሰልጣኝ አንተነህ ጎበዜ በበኩላቸው የተሻለ ውጤት ያላቸው ስፖርተኞች ተመርጠው በግዮን ሆቴል መዋኛ ገንዳ ልምምድ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

አትሌቶቹ ዝግጅት እንዲጀምሩ የተነገራቸው በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ልምምድ እንድናቆም ማስፍፈራሪያና ዛቻ እየደረሰብን ነው ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ በድጋሚ የአትሌቶች ምርጫ ለማካሄድ እንደሚፈልግ በመግለጽ ልምምድ እንድናቆም አሳስቦናል ነው ያሉት።

ይህም ለስነ ልቦና ጫና እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።

ሁኔታው "የፌዴሬሽኑ ሰዎች ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ቡድን ጋር አብረው ለመሄድ የእርስ በእርስ ሽኩቻ ውስጥ መግባታቸውን በግልጽ ያመላክታል" ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በመነጋገር ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም