የአገሪቱን የስራ ሁኔታ ለመቀየር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለላቀ ውጤታማነት መነሳሳት ይገባቸዋል - ጠቅላይ ሚኒስትሩ

70
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 የአገሪቱን አጠቃላይ የስራ ሁኔታ ለመቀየር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለላቀ ውጤታማነት መነሳሳት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ በቀጣይ የሚከተሉትን አሰራር በተመለከተ ዛሬ ለአዲሱ ካቢኔያቸው ገለጻ አድርገዋል። የገለጻ ጽሁፉ የስራ አፈጻጻም ውጤታማነት ሂደቶችና መለኪያዎች ላይ የተኮረ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት አሰራሮቹ ውስጥ የነበሩ ግድፈቶችም ተዳሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው ራዕይ ማስቀመጥ፣ ወጥ የሆነ የአሰራር እሴት መገንባትና የጊዜና ሃብት አጠቃቀም ለስኬታማነትና ተሽሎ ለመገኘት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፉት አንድ ወር በተለያዩ አካባቢዎች ከህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት አገራዊ ስሜት እየጠፋ፣ መራራቅና ነገሮችን ከራስ ዛቢያ ብቻ መመልከት መጉላቱን መገንዘባቸውንና ይህም አገርን አደጋ ላይ እንደሚጥል አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት ያለውን መነቃቃትና ተስፋ ለማስቀጠል በርካታ ስራዎች ይጠብቁናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮችን ለመፍታት የተለመደውን አሰራር መከተል ዋስትና አይሆንም ብለዋል። ችግሮቹን ለመፍታት በተሻለ ዘዴና ቅልጥፍና ስራዎችን ማከናወን መፍትሄ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም