ለ2 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት ለወጣው ጨረታ 6 ድርጅቶች ሰነድ አስገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለ2 የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት ለወጣው ጨረታ 6 ድርጅቶች ሰነድ አስገብተዋል
አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 18/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለሁለት አዳዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት በወጣው ጨረታ ስድስት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ድርጅቶች ሰነድ ማስገባታቸውን የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የጨረታ ማስገቢያው ጊዜ ዛሬ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ከ5 ሰዓት ጀምሮም የጨረታ ሰነዱን የመክፈት መርሃ-ግብር ተካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ለሁለት አዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ ባወጣው ጨረታ ለመሳተፍ 6 የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ አስገብተዋል፡፡
በዚህም ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ በተባለ ተቋም ስም ሳፋሪኮም ከኬንያ፣ ቮዳፎን ከብሪታኒያ፣ ቮዳኮም ከደቡብ አፍሪካ፣ ሲ.ዲ.ሲ ግሩፕ ከብሪታኒያ እና ሰሚቶሞ ኮርፖሬሽን ከጃፓን በጥምረት እንዲሁም ኤም.ቲ.ኤን ከደቡብ አፍሪካ ሰነዳቸውን ያስገቡ ድርጅቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ፈቃድ አሸናፊዎች ባለሥልጣኑ በተረከባቸው የጨረታ ሰነዶች ላይ የሚያከናውነውን የቴክኒክ እና የፋይናንስ ግምገማዎች ካጠናቀቀ በኋላ የሚገለፅ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከኢትዮ-ቴሌኮም በተጨማሪ ለሁለት ኩባንያዎች የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያ አውጥቶ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም 12 የቴሌኮም ድርጅቶች በጨረታው ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን አሳይተው እንደነበር የገለጹት ዳይሬክተሩ ከድርጅቶቹም መካከል የተቀመጠውን የቴክኒክ እና የፋይናንስ መስፈርት ያላሟሉ ድርጅቶች በመመዘኛው መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ፍላጎት ካሳዩ 12 ድርጅቶች መካከል ስድስቱ አስፈላጊውን መስፈርት ያሟሉ በመሆኑ ለጨረታው መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ብቸኛው የቴሌኮሙዩኒኬሽን ፈቃድ ያለው ኢትዮ- ቴሌኮም ነው፡:
የቴሌኮም ዘርፉ ላይ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ መንግሥት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከያዛቸው እቅዶች መካከል አንዱ ነው፡፡