ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው - የፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው - የፌዴሬሽን ምክር ቤት
ሚያዚያ 18/2013 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠየቀ።
የምርጫ ካርድ በመውሰድና በምርጫው በመሳተፍ ዜጎች ህገ-መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን መብት እንዲጠቀሙም ጥሪውን አስተላልፏል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚያከናውናቸው ልዩ ልዩ ተግባራት በተጨማሪ መንግስት እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።
የፌዴራልና የክልል መንግስታትም ይህን ተገንዝበው የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ነው ያሳሰቡት አፈ ጉባኤው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የህገ-መንግስቱ የበላይ ጠባቂ እንደመሆኑ ምርጫ ህገ-መንግስቱ ባስቀመጠው አግባብ እንዲሄድ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም አብራርተዋል።
በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለህዝብ በማቅረብ ድምጽ ለማግኘት መፎካከር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
ምርጫውን በማሸነፍ ወደ ስልጣን የሚመጣው አካል ደግሞ ለህዝቡ ቃል የገባውን በአግባቡ ለመፈጸምና የህገ-መንግስቱን የበላይነት ማስከበር ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሀገርን ማሻገር የሚቻለው የፉክክርና የትብብርን ሚዛን ጠብቆ በመሄድ መሆኑን አስገንዝበው፤ ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዜጎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በምርጫው በመሳተፍ ህገ-መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን መብት እንዲጠቀሙም አፈጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል።
6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮች ደግሞ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።
የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።