ቀጥታ፡

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዘገቡ

ሚያዚያ 18/2013/ ኢዜአ/ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዘግበዋል።

በአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን /ሲኤቪቢ/ አስተናጋጅነት 32ኛው የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ከሚያዚያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በቱኒዚያ እየተካሄደ ነው።

በውድድሩ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ነው።

ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ሁለቱም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ክለቦች በውድድሩ የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

በምድብ ሁለት የሚገኘው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ  በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቡርኪናፋሶውን ኤስ ዱዋኔስ 3 ለ 1 አሸንፏል።

የአፍሪካ ቮሊቦል ኮንፌዴሬሽን በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በመጀመሪያ ተሳትፎው የመጀመሪያ ድሉን በማስመዝገብ ኢትዮጵያን አኩርቷል ሲል ገልጿል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ በምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታውን ዛሬ ከኮትዲቯሩ አሴክ ሚሞሳስ ጋር የሚያደርግ ሲሆን ክለቡ በምድቡ ያደረጋቸውን የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች መሸነፉ ይታወሳል።

በሌላ በኩል በምድብ አንድ የሚገኘው ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና የቡሩንዲው ሙዚንጋ ጨዋታቻውን ማድረግ ነበረባቸው።

ይሁንና የሙዚንጋ ክለብ ተጫዋቾች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭነት ምክንያት ጨዋታውን ማድረግ እንደማይችሉ በመረጋገጡ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በፎርፌ ማሸነፉን ኮንፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊት በምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በቱኒዚያዎቹ ሲኤስ ሰፋክሲያንና ኬሊቢያ ክለቦች መሸነፉ የሚታወስ ነው።

ክለቡ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ከኬንያው ኬንያ ፕሪዝንስ ጋር ያደርጋል።

የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለብ ውድድር እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ይቆያል።

በተያያዘ ዜና 39ኛው የአፍሪካ የወንዶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ከሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተመሳሳይ በቱኒዚያ እየተካሄደ ይገኛል።

ኢትዮጵያን ወክሎ በውድድሩ እየተሳተፈ ያለው ወላይታ ዲቻ በነበረበት ምድብ ባካሄዳቸው ሶስት ጨዋታዎች በቱኒዚያ ኬሊቢያ፣ በታንዛኒያው ኤምቲሲና በዩጋንዳው ኔሞ ስታርስ መሸነፉ ይታወሳል።

ከ9-16ኛ ደረጃን ለማግኘት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎችም በሩዋንዳው ሩዋንዳ ኢነርጂና በቡሩንዲው ሩኪንዞ ክለቦች ሽንፈት ገጥሞታል።

እስካሁን ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች የተሸነፈው ወላይታ ዲቻ 15ኛ እና 16ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ዛሬ ከኮትዲቯሩ ኤስኦኤ ክለብ ጋር ይጫወታል።

በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ትናንት በተደረጉ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ሌላኛውን የቱኒዚያ ክለብ ኬሊቢያ እንዲሁም የግብጹ ዛማሌክ የሊቢያውን ስዌህሊም በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፈዋል።

የቱኒዚያው ኤስፔራንስና የግብጹ ዛማሌክ የፍጻሜ ጨዋታቸውን ነገ ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም