የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አገራዊ አንድነትና የሕዝቦች መከባበርን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል - የፌዴሬሽን ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አገራዊ አንድነትና የሕዝቦች መከባበርን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል - የፌዴሬሽን ምክር ቤት
አዲስ አበባ ፣ሚያዚያ 17/2013 (ኢዜአ) 16ተኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና የሕዝቦችን መከባበር በሚያጎለብት መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።
ምክር ቤቱ በመጪው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር አስመልክቶ በተዘጋጀው መሪ እቅድ ላይ ከክልል ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎችና ከበዓሉ አስተባባሪ አብይ ኮሚቴ ተወያይቷል::
በዓሉ የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር በማጠናከር በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ሕብረብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት እንደሚከበር የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ ገልጸዋል።
ከቀደመው ጊዜ በተለየ ሕዝቦችን የሚያስተሳስሩ ትርክቶችን በማጉላትና 'አንዳችን ለሌላችን እንደምናስፈልግ በማሳየት ይከበራል' ሲሉም ተናግረዋል።
የሕዳሴ ዋንጫ ርክክብ፣ አገር አቀፍ ሲምፖዚየም፣ የሕገ መንግስትና የፌዴራሊዝም አስተምህሮ፣ የባሕል ትርዒትና ኤግዚቢሽን፣ የደም ልገሳና የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ከበዓሉ ሁነቶች መካከል ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የበዓሉ አከባበር ሁነቶች የአገርና የሕዝቦችን አንድነት በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ያተኮሩ መሆን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የክልል ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎችና የአብይ ኮሚቴው አባላትም ከምርጫና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች አንጻር ለቀጣዩ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከወዲሁ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለዚህም ከዚህ ቀደም በበዓሉ ያልተካተቱ ነገር ግን ቢኖሩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ከማጎልበትና ከማጠናከር አኳያ ሚና ይኖራቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮችም አንስተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ በበዓሉ ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ኡጋዞች የሚሳተፉበት መድረክ ቢፈጠር ሲሉም ሃሳብ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው በበዓሉ የሚካተቱ ተግባራት ከአሁን ጀምሮ መከናወን ቢጀምሩ ሲሉ ተናግረዋል።
በተለይ የሲምፖዚየሞች መድረኮች ከወዲሁ ቢጀመሩ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ይበጃል ብለዋል።
በመድረኩ የተነሱ ሃሳቦች ለ16ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል መሪ እቅድ በግብዓትነት በመውሰድ መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ የሚደረግ መሆኑን አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ ገልጸዋል።
ለ16ተኛው የብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የተለዩ ሶስት መሪ ሃሳቦች ለተወያዮቹ ቀርበው ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
የተሻለ ገላጭ የሚሆነው መሪ ቃል በሂደት ከቋንቋ ምሁራን ጋር በመመካከር እንደሚወሰን አፈ-ጉባዔው አስታውቀዋል።
16ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የማጠቃለያ መርሃ ግብር በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንደሚካሄድ ተገልጿል።