ቀጥታ፡

በትግራይ ስልጠና የተሰጣቸው 1ሺህ 100 በጎ ፍቃደኞች ተመረቁ

መቀሌ ፣ ሚያዝያ 17/2013 (ኢዜአ) የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰላም ሚኒስትር ጋር በመተባበር ለአንድ ወር ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 100 በጎፈቃደኛ ወጣቶች ዛሬ አስመረቀ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እንዳሉት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለችግር ለተጋለጡ የክልሉ ህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ድጋፍ በማድረግ ወገናዊነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል።

ሰልጣኞቹ የተለያዩ ተፅእኖዎችን በመቋቋም ወደ ስልጠናው መምጣታቸውን የገለጹት ዶክተር ሙሉ ወጣቶቹ ህብረተሰቡን ካጋጠመው ችግር ለማውጣት እየተደረገ ባለው ጥረት ያቅማቸውን ለማበርከት በመወሰናቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።

ወጣቶች ባሉባልታና በጊዜያዊ ችግሮች ሳይወድቁ ጊዜያቸውን በበጎ ተግባራትና ለቀጣይ ህይወታቸው መሰረት በሚጥል መልኩ በማሳለፍ የልማት ተቋዳሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ስልጠናው አስተማሪ መሆኑን ዶክተር ሙሉ ጠቁመዋል።

በጎ አገልግሎት በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም በስፋት እንደሚሰራበት የተናገሩት ዶክተር ሙሉ ወጣቶች ህብረተሰቡን ለማገልገል በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ለቀጣይ ህይወታቸው መሰረት እየጣሉ መሆናቸውን አውቀው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

ሰልጣኝ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ለአስር ወራት በየአካባቢያቸው ተሰማርተው በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ዶክተር ሙሉ አስታውቀዋል ።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስማ ረዲ በበኩላቸው ለአሁኑ የተመራቂ ወጣቶች የተሰጠው ስልጠና ተቋማቸው በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስራ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ለአንድ ወር ያህል በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በተሰጠው ስልጠና ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተውጣጡ 1ሺህ 100 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሳተፋቸውን ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው ስለ በጎ ፈቃደኝነት ምንነትና አስፈላጊነት፣ ስለ ስራ አመራር አስተዳደር፣ የስራ ፈጠራ ክህሎትና በሽርክና የመስራት አስፈላጊነት በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን አመልከተዋል ።

ሰልጣኞች በተለያዩ ወቅቶች ከዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው ስራ ያላገኙ ወጣቶች እንደሆኑና የማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው ስለመሆናቸው የስልጠናው አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።

ከተመራቂ ሰልጣኞች መካከል በነርሲንግ ሙያ በ2011 ዓ.ም ከዩኒቨርስቲ መመረቋን የተናገረችው ወጣት ፍጹም መሃሪ ህብረተስቡን ለማገልገል በመዘጋጀቷ ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች።

ከደቡባዊ ዞን ከመሆኒ ከተማ የመጣው ወጣት ዝናቡ ካልአዩ በበኩሉ በኤሌትሪካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ ስራ ያልነበረው መሆኑን ገልጿል።

በተሰጠው ስልጠና ክልሉ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ማግኘቱን ጠቅሶ በስልጠናው ባገኘው ግንዛቤ በመታገዝ በትምህርት በቀሰመው ሙያ ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም