ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ ጽንፈኛ ሃይሎችን እንታገላቸዋለን - የያቤሎ ወረዳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ ጽንፈኛ ሃይሎችን እንታገላቸዋለን - የያቤሎ ወረዳ ነዋሪዎች
ነገሌ፣ ሚያዝያ 17/2013 (ኢዜአ ) ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ ጽንፈኛ የጥፋት ሃይሎችን ከመንግስት ጎን በመሆን እንታገላቸዋለን ሲሉ በቦረና ዞን የያቤሎ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ነዋሪዎቹ በህግ የበላይነት፣ በዘላቂ ሰላምና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትላንት በያቤሎ ከተማ ከመንግስት አመራሮች ጋር መክረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ከተሳተፉ የወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ ጃተኒ ሞሉ ባነሱት ሐሳብ የኦሮሞ ህዝብ በመከባበርና በመቻቻል ከሁሉም ብሄር ብሔረሰቦች ጋር የተዋለደና የተጋመደ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
"ጽንፈኞች ሀገር የማፍረስ ተልእኳቸውን ለማስፈጸም ሰሞኑን በአማራ ክልል የጀመሩት የጥፋት ዘመቻ የሁለቱንም ክልል ህዝቦች አይወክልም ብለዋል፡፡
"በጥፋት ተልእኮ ፈጻሚዎች ከንቱ ምኞትና ፍላጎት ሀገር እንዳይፈርስ ከመቸውም በላይ ከመንግስት ጎን በመሆን እንታገላለን" ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ሰብስቤ ጉልማ በበኩላቸው የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የጥፋት ሃይሎችን ከማጋለጥ ሌላ ምርጫ እንደሌለ አመልክተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ መንግስት ያሳየው ከልክ ያለፈ ትእግስት ለጽንፈኞችና ለጥፋት ሃይሎች እድል መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡
በጥላቻ ንግግር ብሄር ከብሄር በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ በሚሰሩ ጽንፈኛ ሃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድና ውጤቱን ለህዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
"መንግስት የህግ የበላይነትን እያስከበርኩ ነው ቢልም አሁንም በብሄር ሽፋን በሚደርስ ጥቃት የዜጎች ሞት፣ ስደትና መፈናቀል አልቆመም" ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አቶ ጉዮ ዶዮም ናቸው፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለማስቆምና የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት ከህዝብ ጋር ተባብሮ ከመስራት በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡
የምክክር መድረኩን የመሩት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጉዮ ቃሊቻ "የስልጣን ጥመኞች የሚለቁት የጥላቻ ንግግር ከመጠፋፋት ሌላ ለውጥ አያመጣም" ብለዋል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጎን ለጎን አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ከሰላም ወዳዶች ጋር በትብበር እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሰላምና ልማት በማይፈልጉ ሃይሎች ላይ መንግስት የማያዳግም ህጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡
የጥፋት ተልእኮ የተቀበሉ ጽንፈኞችንና የጥፋት ሃይሎችን በማጋለጥ የወረዳው ህዝብ ሀገር ለማዳን የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የወረዳው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡