ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በምዕራብ አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ600ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ

ሚያዚያ 17 /2013 (ኢዜአ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት በምዕራባ አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ከ600ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰቡ ተገለጸ።

በሎስ አንጀለስና አካባቢው የሚኖሩ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የልዑካን ቡድን ከልዩ ልዩ አደረጃጀት ተወካዮች ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን ማገዝ በሚችሉበት ዙሪያ ተወያተዋል።

በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባስተላለፉት መልዕክት በሎስ አንጀለስና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመደገፍ እያከናወኑ ስላሉት አርአያነት ያለው ተግባር አመስግነዋል፡፡

ይኸው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሀገሪቱ ከዳያስፖራዋ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በላቀ ደረጃ ማግኘት እንዲችል ኤጀንሲው ከዳያስፖራው ጋር ተቀራርቦ መስራቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም በአጭር ጊዜ ውስጥ በተከናወኑ የንቅናቄ ስራዎች ከዳያስፖራው ማሰባሰብ የተቻለው ከፍተኛ የሀብትና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ድጋፍ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ዕምቅ አቅም ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

አብነቶችን በመጥቀስ ያብራሩ ሲሆን፣ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል በዳያስፖራው ዘንድ የሚታየውን መነሳሳት አድንቀዋል፡፡

በሎስ አንጀለስ የኢፌዴሪ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል በበኩላቸው ዳያስፖራው ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችም ሆነ ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በምዕራባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ብቻ ከ600ሺ ዶላር በላይ መሰብሰቡን ገልጸው፣ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያሳይና ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ባነሷቸው ጥያቄና አስተያየቶች ላይ ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በተሳታፊዎች ከተነሱ ሃሳቦች መካከል የተጠናከረ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የአድቮኬሲ ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ ከዳያስፖራው የሚገኘውን ድጋፍ ማሳደግ የሚችሉ ተጨማሪ የሀብት ማሰባሰቢያ መንገዶች መመቻቸት እንዳለባቸው፣ ሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ አባላትን ከሃገራቸው ጋር የሚያስተሳስር አሰራር ሊፈጠር እንደሚገባ፣ የበጎ አድራጎት ተግባራትን በቀላሉ ማከናወን የሚቻልባቸው አሰራሮች መመቻቸት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

ኤጀንሲው ዳያስፖራውን ከሀገሩ ጋር ለማስተሳሰር የጀመራቸውን አበረታች ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ፣ ለግጭትና ለዜጎች ህይወት መጥፋት መነሻ የሆኑ ምክንያቶች ሊለዩና መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ፣ ዳያስፖራው ያስተማረችውን ሀገሩን የመካስ ዕዳ እንዳለበትና ሀገሩን ለመደገፍ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ እንደሌለበት እንዲሁም የጥምር ዜግነት ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርና አምባሳደር ባስተላለፉት መልዕክት ዳያስፖራው በተቻለው አቅም ሁሉ ሀገሩን ለመደገፍ ስለሚያሳየው ተነሳሽነትና እያከናወናቸው ስላሉ ተጨባጭ ስራዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ቀጣይ ዳያስፖራው በሀገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ምክንያት የሆኑትን ውስጣዊና ውጫዊ መንስኤዎች ተረድቶና ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ላይ ያለች መሆኗን ተገንዝቦ የለውጥ ሂደቱ እንዲሰናከል የሚፈልጉ ሃይሎች ባዘጋጁት ወጥመድ ውስጥ ሳይገባ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ በድል ማለፍ እንዲቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም