ኢትዮጵያ የወባ በሽታን በመከላከል ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የወባ በሽታን በመከላከል ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘች
ኢትዮጵያ በኮቪድ ወቅት የወባ በሽታ ጉዳት እንዳያደርስ በሰራችው ስራ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ዕውቅና ማግኘቷን የጤና ሚኒቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ዓለምአቀፍ የወባ ቀንን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
ኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚሆነው አካባቢዋ ለወባ ስርጭት አመቺ ሲሆን 52 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ባለፈው ዓመት የወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ 44 በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ ወደ 57 በመቶ በመቀነስ ከዕቅድ በላይ በመስራት ውጤት ማስመዝገቧን መረጃዎች ያሳያሉ።
በመግለጫው ወቅት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት ኢትዮጵያ በኮቪድ ወቅት የወባ በሽታን ለመከላከል ያደረገችው ጥረት የሚበረታታ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተላላፊ የሆኑና ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ፈትኗል።
ይሁንና ችግሮችን በመቋቋም በተሰራው ስራ ባለፈው ዓመት በወባ በሽታ ሳቢያ የሚከሰት ህመምን መቀነስ መቻሉን ጠቁመዋል።
በተለይ በዚህ ወቅት መሰረታዊ የሆኑ የወባ መከላከል አገልግሎቶች ሳይቋረጡ በመሰራታቸው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ዕውቅናን አግኝታለች ብለዋል።
ለጋሽ ድርጅቶቹ ኢትዮጵያ ለያዘችው የአምስት አመት እቅድ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንና ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ2030 ኢትዮጵያ በወባ በሽታ የሚከሰተውን ህመምና ሞት ለማስቀረት እቅድ ነድፋ እየሰራች መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተጀመሩ ስራዎች በተለይ ግብአቶች በወቅቱና በተሟላ ሁኔታ እንዲቀርቡ በማድረግ እንዲሁም የክትትልና ግምገማ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጠሉ አሳስበዋል።
በተለይ በአገሪቱ የወባ በሽታ በአብዛኛው የሚከሰተው በክረምት ወቅት በመሆኑ በመጪው ጊዜ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፍ የወባ ቀን የሚከበረውም ወባን በአገር ደረጃ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ለማሳሰብና የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ኢስተር ማሪአሲንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የወባ በሽታን ለመከላከል ያደረገችው ጥረት ውጤታማ ነው ብለዋል።
በተለይ ኮቪድ 19 የአገራት ስጋትና ትኩረታቸው በሆነ ሰዓት ኢትዮጵያ የመከላከል ስራዋን በማጠናከር ለሌሎች አርአያ የሚሆን ተግባር አከናውናለች ነው ያሉት።
ድርጅቱ ኢትዮጵያ ወባን ጨርሶ ለማጥፋት የምታደርገው ጥረት እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።
የወባ ቀን በነገው ዕለት በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ ''ወባን ማጥፋት ከእኔ ይጀምራል'' በሚል መሪ ቃል ይከበራል።