ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ በይርጋለም ፤ ኢዜማ ደግሞ በዲላ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሄዱ

ሀዋሳ/ዲላ፤ ሚያዝያ 16/2013 (ኢዜአ) ብልጽግና ፓርቲ በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ደግሞ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዱ።

ብልፅግና ፓርቲ  የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያካሄድ የይርጋለም እንዲሁም የዳሌ እና የዎንሾ ወረዳዎች ደጋፊና አባላት ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት  የብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት የከተማ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ኤልያስ፤ ኢትዮጵያ ከሥጋት ወጥታ አሁን ወዳለችበት የለውጥ ጎዳና ያቀናችው በለውጡ መሪዎች መሆኑን ተናግረዋል።

ብልጽግና በቀጣይም ህብረ ብሔራዊ ፌደራልዝም የሰፈነባትና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት የሚሰራ ፓርቲ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ብልፅግናን ለመምረጥ ከሚያደርጉት ዝግጅት ባለፈ ምርጫው ፍትሐዊ፣ ተአማኒና ሠላማዊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የፓርቲው ጽህፈት ቤት የይርጋለም ከተማ ከፍተኛ አመራር  አቶ ደረሰ አለሙ በበኩላቸው  27 ዓመታት ለይስሙላ ሳይሆን በሀገሪቱ እውነተኛ ፌዴራልዝም ተግባራዊ ሆኖ ሲዳማ ራሱን በራሱ ማስተዳደር የቻለው በብልፅግና አመራር መሆኑን ተናግረዋል።

ብልፅግና የሀገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት አቅፎ በማስተባበር ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማሻገር እውነተኛ ብርሀን ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።

ከፓርቲው ደጋፊዎች  መካከል  አቶ ሆሳዕና ዘነበ በመራጭነት ተመዝግበው ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ብልፅግና ፓርቲን ለመደገፍ ካስቻላቸው ምክንቶች መካከል በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜጎች በነፃነትና ፍትሀዊነት በተሞላበት አኳኋን ይመራናል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጡ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ጠቅሰዋል።

አቶ ፀጋዬ ስምዖን በበኩላቸው በሀገሪቱ የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያ ካደጉት ሀገራት እኩል እንድትሆን በመፈለግ ብልፅግና ፓርቲን እስከመጨረሻው እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/   የምርጫ ቅስቀሳ በህዝባዊ መድረክ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ባካሄደበት ወቅት የፓርቲው  ዋና ፀሐፊ አቶ አበበ አካሉ  እንዳሉት  የዞኑ ህዝብ ከምርጫ በላይ ለሰላምና ድህንነቱ በጋራ መስራት አለበት።

ይወክለኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጹን እንዲሰጥና እንዳይጨበረበር ዘብ መቆም እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከሰላሳ ዓመታት በላይ የዘር ፖለቲካ በኢትዮጰያ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

የዜጎች በሀገሪቱ የትም ቦታ ተዘዋውሮ የመኖርና ሃብት የማፍረት መብት እንዲረጋገጥም የዞኑ ነዋሪዎች ካርድ በመውሰድና ኢዜማን በመምረጥ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

እኔ ኢዜማን የተቀላቀልኩት ነጻ ሀገር ለልጆቼ ለማውረስ ነው ያሉት ደግሞ በፓርቲው የሴቶች ተወካይ ወይዘሮ ራሄል አሰፋ ናቸው።

የሴቶች የፖሊቲካ ተሳትፎ ከማረጋገጥ ባለፈ የትም ቦታ ያለስጋትና ያለአድልዎ ተዘዋውሮ ለመስራትና ለመኖር ፖርቲው አመራጭ ሀሳብ ይዞ መቅረቡን አስረድተዋል።

የኢዜማ የጌዴኦ ዞን ተወካይ አቶ ደሳለኝ ደያሶ በበኩላቸው፤ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

ዜጎች የምርጫ ካርድ በመውሰድ ይወክለኛል ላሉት ፓርቲ ድምጽ ከመስጠት ባለፈ የሰጡት ድምጽ እንዲከበር በምርጫው በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁላቸውም በያሉበት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም  አሳስበዋል።

በመድረኩም ፓርቲው በዞኑ ለክልልና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ያቀረባቸውን ዕጩዎች  አስተዋውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም