የቼስ ግራንድ ማስተር እፍስትራቲዮስ ግሪቫስ ለኢትዮጵያ የቼስ ብሔራዊ ቡድን አባላት ስልጠና መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የቼስ ግራንድ ማስተር እፍስትራቲዮስ ግሪቫስ ለኢትዮጵያ የቼስ ብሔራዊ ቡድን አባላት ስልጠና መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010 ግሪካዊው የቼስ ግራንድ ማስተር እፍስትራቲዮስ ግሪቫስ በ43ኛው የቼስ ኦሎምፒያድ ለሚሳተፉት የኢትዮጵያ የቼስ ብሔራዊ ቡድን አባላት በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ትናንት ስልጠና መስጠት ጀምሯል። በጆርጂያ ባቱሚ ከተማ 43ኛው የቼስ ኦሎምፒያድ ከመስከረም 13 እስከ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል። በጆርጂያ ባቱሚ ከተማ በሚካሄደው የቼስ ኦሎምፒያድ በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያንን የሚወክሉ የቡድኑን አባላት ለመምረጥ የተዘጋጀው የግል የበላይነት ሻምፒዮና ከሐምሌ 10 እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ መካሄዱ የሚታወስ ነው። በዚሁ መሰረት በሴቶች ልደት አባተ፣ ፌቨን ገብረመስቀል፣ ሩት ለይኩን፣ መርሃዊት ብርሃነና አስቴር መላክ፤ በወንዶች ደግሞ ብርሃኔ ገብረሚካኤል፣ ግሩም ተክለወልድ፣ ሐፍቶም ገብረመድህን፣ አቤል ማቲዎስና አይዳኙም ግዛቸው ተመርጠዋል። ለጆርጂያው ውድድር የተመረጡት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቅድመ ዝግጅት የሚረዳ ስልጠና ግሪካዊው የቼስ ግራንድ ማስተር እፍስትራቲዮስ ግሪቫስ መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ ገልጸዋል።በቼስ ኦሎምፒያዱ ጥሩ ተሳታፊና ተፎካካሪ ስፖርተኞችን ከወዲሁ ለማዘጋጀት ለዓለም አቀፉ ቼስ ፌዴሬሽን ስልጠና እንዲያመቻችላቸው በቀረበው ጥያቄ መሰረት ግሪካዊው የቼስ ግራንድ ማስተር ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ጠቁመዋል። የቼስ ግራንድ ማስተሩ ለቼስ ብሔራዊ ቡድኑ አባላት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና የሚሰጡ ሲሆን ተጫዋቾቹ መልካም ተሞክሮ በማግኘት አቅማቸውን ከማሳደግ አንጻር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። እፍስትራቲዮስ ግሪቫስ በዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን እውቅና ከተሰጣቸው አሰልጣኞች አንዱ እንደሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቼስ ውድድሮች ውጤታማ ጊዜ ያሳለፈ እንደሆነ ነው አቶ ሰይፈ ያስረዱት። ስልጠናው እስከ ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። የ52 ዓመቱ የቼስ ግራንድ ማስተር እፍስትራቲዮስ ግሪቫስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተዋቂ የቼስ ክለቦችን ያሰለጠነ፣ በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ በቼስ ስፖርት ትንተና የሚሰጥና በቼስ ስፖርት ዙሪያ መጽሐፎችን በመጻፍ ለስፖርት አፍቃሪው እንዲደርስ አድርገዋል። የቼስ ግራንድ ማስተርነት የዓለም አቀፉ የቼስ ፌዴሬሽን (ፊዴ) የቼስ ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያስመዘግቡት ውጤትና በሚኖራቸው ስፖርታዊ ጨዋነት የሚሰጣቸው ከፍተኛ ማዕረግ ነው። የዓለም አቀፉ የቼስ ፈዴሬሽን እስካሁን ለ1500 የቼስ ስፖርተኞች የግራንድ ማስተርነት ማዕረግ ሰጥቷል።