በቢሾፍቱ የተገነባው የእንስሳት መድኃኒት ፋብሪካ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በቢሾፍቱ የተገነባው የእንስሳት መድኃኒት ፋብሪካ ተመረቀ
ሚያዚያ 16/2013 (ኢዜአ) ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በቢሾፍቱ ከተማ ያስገነባው የእንስሳት መድኃኒት ፋብሪካ ተመረቀ።
ፋብሪካው የእንስሳት ሀብት ለአገር ኢኮኖሚ የሚያደርገውን አስተዋፆ ከማሳደግ በተጨማሪ ለመድሃኒት ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት የሚረዳ መሆኑ ተገልጿል።
የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በ1956 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 23 አይነት ክትባቶችን ያመርታል።
ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማርታ ያሚ ለ35 አመታት ክትባቶቹን በነፃ ሲያቀርብ እንደቆየና ላለፉት 22 አመታት ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለግብርናው ዘርፍ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
ለተለያዩ አገራት የእንስሳት ክትባቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በክትባት ዙሪያ ምርምርና ጥናቶችን እየሰራ መሆኑንም ዶክተር ማርታ አብራርተዋል።
በዛሬው እለት ያስመረቀው ፋብሪካም የግብርናውን ዘርፍ ከመደገፍ በተጨማሪ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለፋብሪካው ግንባታ፣ መሳሪያ ግዢና ገጠማ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንዳወጣበት ገልፀው 12 አይነት የተለያዩ የእንስሳት መድሃኒቶችን በማምረት ለገበያ ማቅረብ ይችላል ብለዋል።
ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ወደስራ ለመግባት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግር እንደሆነበትና ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን እንዳሉት "ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአለም ስድስተኛ ከአፍሪካ አንደኛ ብትሆንም" ምርትና ምርታማነቱ ዝቅ ያለ መሆን ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያበረክት አድርጎታል።
የእንስሳት ስጋ ወደ ውጭ በሚላክበት ወቅት ከጥራቱ ይልቅ ጤንነቱ ይታያል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህም ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብት ማግኘት የሚገባትን እንዳላገኘች ተናግረዋል።
ለምርታማነቱ መቀነስ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ የእንስሳት በሽታ አንዱ መሆኑን ገልፀው ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት በአገሪቱ ያሉ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ክትባቶችን በማምረት የእንስሳት ሀብት ለአገር ኢኮኖሚ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ፋብሪካው የእንስሳት ሀብት ለኢንዱስትሪ ልማት የሚኖረውን አስተዋፆ ከማሳደግ በተጨማሪ የስጋ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች በብዛትና በጥራት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ እገዛ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
ፋብሪካው በዚህ ረገድ ከሚኖረው እገዛ ባሻገር ለሌሎች አገራት ምርቶቹን በመላክ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኝ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠርና አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደ ክትባት ሁሉ መድሃኒቶችንም ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ማድረግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
አቅም ካላቸው ተመሳሳይ የውጭና የአገር ውስጥ የግል ተቋማት ጋር መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደማምረት እንዲገባ ሚኒስቴሩ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የሌሎች ተቋማት እገዛ ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።
መሰል ተቋማትን ለማጠናከር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ በጋራ ከኢንስቲትዩቱ ጋር መስራት አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።
የፋብሪካው ግንባታ በህዳር 2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ፋብቴክ አለምአቀፍ ቴክኖሎጂ የተሰኘ የህንድ ኩባንያ ግንባታውን አከናውኖታል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ለፋብሪካው መጠናቀቅ አስተዋፆ ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት የእውቅና የምስክር ወረቀትና ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል።