የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደቱ ሳይስተጓጎል ትምህርት ይቀጥላል- ዩኒቨርሲቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደቱ ሳይስተጓጎል ትምህርት ይቀጥላል- ዩኒቨርሲቲዎች
ሚያዚያ 16/2013 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳይስተጓጎል ጥንቃቄዎችን በማድረግ ትምህርት መስጠት እንደሚቀጥል የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የጥንቃቄ እና የመከላከል ስራ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱን አስመልክቶ ኢዜአ የተለያዩ ዩኒቨርሰቲዎች ፕሬዚዳንቶችን አነጋግሯል።
የአዲስ አበባ፣ አርባምንጭ፣ ሐሮማያ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በወረርሽኙ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ቅድመ መደበኛ አሁን ላይ የገጽ ለገጽ ትምህርትን ከኦንላይን ትምህርት ጋር በማቀናጀት ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ወረርሽኙ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር እና የመማር ማስተማር ሂደቱም ሳይስተጓጎል ለመስጠት እንዲቻል በተማሪዎችና በሌሎችም የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቦች አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ትምህርት መስጠት የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
ትምህርቱ በሚሰጥበት ወቅትም በተለይ ወረረርሽኙን በመከላከል ረገድ ተማሪዎች ግንባር ቀደም ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ተማሪዎችና ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቦች በጤና ሚኒስትር የወጡ የኮቪድ-19 መከላከያ ፕሮቶኮሎችን በመተግበር ራሳቸውን ከበሽታው እየተከላከሉ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ማድረግ፣ ርቀትን በመጠበቅ፣ የግል፣ የመኝታ፣ የመማሪያ እና የመመገቢያ ክፍሎችን ንጽህና በመጠበቅ ወረርሽኙን በመከላከል እንዲማሩ ይደረጋልም ብለዋል።
በዚህ ረገድም ቅድሚያ የግንዛቤ ስራ ዋነኛ በመሆኑ ተማሪዎች ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳቸውንም ሆነ ሌላውን ማህበረሰብ እንዲጠብቁ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሌላው ህብረተሰብ በተሻለ መልኩ በግንዛቤ እና መረጃዎችን ለማግኘት ቅርብ የሆኑ ከመሆናቸው አኳያም ለሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ወረርሽኙ እየተስፋፋ እየመጣ ከመሆኑ አንጻር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የጥንቃቄ መንገዶች እንዲተገበሩ ጠንካራ ክትትል የሚያደርጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የመከላከል ተግባሩን በማጠናከርም በተማሪ አደረጃጀቶች፣ በተማሪ ህብረት፣ በሰላም ፎረም፣ በስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚቴዎችና በሎችም አደረጃጀቶች የግንዛቤና የክትትል ስራ የሚጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገጽ ለገጽ ትምህርት እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።
ይህም መስከረም ወር በጅማ ከተማ በተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶችን በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እንዲቀጥል መወሰኑ የሚታወስ ነው።
በዚህም ካለፈው ከጥቅምት ወር 2013 ዓ ም ጀምሮ ተማሪዎች ወደየዩኒቨርሲቲዎቻቸው ገብተው ትምህርት እየተከታተሉ ይገኛሉ።