በመዲናዋ የሚኖሩ መስማት የተሳናቸዉ ዜጎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ወስደው ማሽከርከር ሊጀምሩ ነው

ሚያዚታ 16/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የሚኖሩ መስማት የተሳናቸው ዜጎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ወስደው ማሽከርከር ሊጀምሩ መሆኑን የከተማዋ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ከተማ አስተዳደሩ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን መስማት ለተሳናቸው ዜጎች የአሽከርካሪ ማረጋገጫ ብቃት ማውጣት መቻላቸውን አስመልክቶ የማስጀመሪያ ስነስርዓት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ትዕግስት አለማየሁ እንደገለጹት ከ40 አመታት በላይ ጥያቄ ሲያቀርቡና ሲታገሉለት የነበረው መስማት የተሳናቸው ዜጎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ በመሰጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ 

ብዙ መስማት የተሳናቸውና ችሎታ ያላቸው ዜጎች እንዳሉና ነገር ግን በሲስተም ምክንያት ወደኋላ እንደሚቀሩ ገልጸው መስማት የተሳናቸው ዜጎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ብቃት ወስደው ስራ ሲጀምሩ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር ይችላሉ ብለዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አደም ኑሪ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ቀደም ሲል የነበረውን የህግ ማእቀፍ በማሻሻል መስማት የተሳናቸው ዜጎች ባላቸው እውቀትና ችሎታ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የአሽከርካሪ ፈቃድ የሚወስዱ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ገብተው የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠናዎች እንደሚወስዱም ተናግረዋል፡፡ 

ሰፋፊ የፊትና የኋላ ስፖኪዮ ባላቸውና ድምጽን ወደምስል በሚቀይር ቴክኖሎጂ በታገዘ ተሽከርካሪ እንደሚሰለጥኑ የተናገሩት ደግሞ በባለስልጣኑ የአሽከርካሪ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቅድስት ግዛቸው ናቸው፡፡

ባለስልጣኑ በዛሬው ዕለት አገራዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ 77 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት እና 22 የቴክኒክ ምርመራ ተቋማት የዕውቅና ሽልማት አበርክቷል፡፡

በዓለም ላይ በርካታ አገራት መስማት የተሳናቸው ዜጎች ማሽከርከር አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት እየቀየሩ መምጣታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም