ቀጥታ፡

በአውሮፓዊያኑ የክረምት ወቅት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱሪስቶች ዝግጅት ተደርጓል - ቱሪዝም ኢትዮጵያ

ሚያዚያ 15/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው የአውሮፓዊያኑ የክረምት ወቅት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች በመዝናናት ጥሩ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዝግጅት መደረጉን ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት መጀመሩን ተከትሎ በአውሮፓዊያኑ የክረምት ወቅት የበርካታ ጎብኚዎች እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚችል ተገምቷል።

የአውሮፓ የክረምት ወቅት በአብዛኛው የአውሮፓ አገራት እ.አ.አ ከጁን አስከ ኦገስት (በኢትዮጵያ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ) ያለው ጊዜ ነው።

በዚህ የክረምት ወቅት አውሮፓውያን ወደ ተለያዩ አገራት በመሄድና ጉብኝት በማድረግ ጊዜያቸውን በመዝናናት የሚያሳልፉበት ወቅት እንደሆነም ይነገራል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የቱሪዝም አዝማሚያ ትንተና መሰረት በአውሮፓ የክረምት ወቅት አውሮፓውያውን ኢትዮጵያን የመጎብኘት ዝንባሌ አላቸው።

በተለይም አብዛኛው የስፔን ቱሪስቶች ኢትዮጵያን በሐምሌና ነሐሴ ወራት የመጎብኘት ልምድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት አሁን በሚመጣው የአውሮፓ ክረምት ወቅት በርካታ አውሮፓዊያን ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱሪስቶች በመዝናናት ጥሩ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት በኮቪድ ምክንያት በሚፈለገው መጠን የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ አለመምጣታቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም አሁን ላይ የኮቪድ 19 ክትባት በስፋት እየተከናወነ በመሆኑ የበርካታ ቱሪስቶች እንቅስቃሴ እንደሚኖር ይጠበቃል።

በአውሮፓ የክረምት ወቅት ደግሞ በተለይ ከአውሮፓ አገራት ተጨማሪ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ምቹና ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል። 

በበይነ መረብ የቱሪዝም መደረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉ የሚመራበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፕሮቶኮል ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝና ጉብኝዎችም በዚሁ መመሪያ ይስተናገዳሉ ብለዋል።

በመንግስት በኩል የቱሪስት መዳረሻዎችን ጨምሮ ሆቴሎችና ሌሎች የቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን ጸረ-ኬሚካል ተዋህሲያን በመርጨት ደህንነታቸውን የመጠበቅ ስራ በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በአዲስ አበባ የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለጎብኚዎች ተጨማሪ አማራጮች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በጥር ወር 2013 ዓ.ም ከዓለም የቱሪዝምና የጉዞ ምክር ቤት የጉዞ ደህንነት ማረጋገጫ እውቅና ማግኘቷን አስታውሰው ይሄም አገሪቷ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዳግም ለማስጀመር በሰራቻው ስራዎች የተገኘ ነው ብለዋል።

ይህን እውቅና ተጠቅሞ የውጭ አገር ጎብኚዎችን ለመሳብ የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና እውቅናው ለጎብኚዎች ያላቸውን የራስ መተማመን እንደሚጨምር አስረድተዋል።

በ2013 ዓ.ም በጀት ዘጠኝ ወር ኢትዮጵያ ከ143 ሺህ 502 ጎብኚዎች 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ከባሀልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ300 ሺህ ጎብኚዎች 750 ሚሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የጸጥታ ሁኔታና በወረርሽኙ ምክንያት ከአገር ውጪም ከአገር ውስጥም የአየር በረራ መቀነሱ ለገቢው መቀዛቀዝ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተገልጿል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ክፋኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች መካከል ቱሪዝም በዋነኛነት ይጠቀሳል።

አገራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በጣሉት የጉዞ እገዳዎችና ክልከላዎች ምክንያት እ.አ.አ በ2020 በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራት ሲጠብቋቸው የነበሩ አንድ ቢሊዮን ጎብኚዎች እንዳላገኙና 1 ነጥብ 1 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት የቱሪዝም ገቢ ማጣታቸውን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም አቀፉ የቱሪዝም ተቋም (ዩኤንደብሊውቲኦ) የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም