ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ መስማት የተሳናቸውን ተደራሽ ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት ተገለጸ

ሚያዚያ 16/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መልእክቶቻቸውና የምረጡኝ ቅስቀሳቸው መስማት የተሳናቸውን ተደራሽ ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በምርጫ ፉክክሩ 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉ ሲሆን የምረጡኝ ቅስቀሳና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሚዲያ በመከራከር ላይ ይገኛሉ።

በምርጫ ሂደት የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸው መስማት የተሳናቸውን ተደራሽ ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበት መስማት የተሳናቸው ወገኖች ይናገራሉ።

ምርጫውን በሚመለከት የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም በጎ ፈቃደኛ ማህበር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ በጋራ መስማት ከተሳናቸው ወጣቶች ጋር ምክክር አድርገዋል፡፡

መድረኩ “አንድ ወጣት ለሀገሩ ሰላም ምን ማድረግ ይችላል” በሚል መሪ ሃሳብ የተከናወነ ሲሆን መስማት የተሳናቸው ወጣቶች በምርጫው የሚኖራቸው ተሳትፎ በሚጠናከርበት ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም በጎ ፈቃደኛ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዮሃንስ ጣሰው እንደተናገሩት የመድረኩ ዋነኛ አላማ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በምርጫው የሚኖራቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር ነው።

መድረኩ በተለይ ይጠቅመናል የሚሉትን ፓርቲ በአግባቡ ተገንዝበው ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ወስደው ዝግጅቶች እንዲያደርጉ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም መልእክቶቻቸውንና የምረጡኝ ቅስቀሳዎቻቸውን አካል ጉዳተኞችንና መስማት የተሳናቸውን ዜጎች ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ልማት፣ ዴሞክራሲና ማህበራዊ ተሳትፎ ምን ጊዜም አካል ጉዳተኞችንና መስማት የተሳናቸውን ወገኖች ማእከል ያደረገ መሆን አለበትም ነው ያሉት።

በምክክር መድረኩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ በሚካሄደው ምርጫ በተለይ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን መስማት የተሳናቸውን ታሳቢና ተደራሽ ሊያደርግ ይገባል ብልዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ደሞክራሲያዊና ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን የሀገር ሰላም እንዲሁም የማህበረሰቡ አብሮነትና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም