ቀጥታ፡

ለምርጫው ስኬታማነት ጋዜጠኞች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል…የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት

ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 16/2013(ኢዜአ) ለ6ኛው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ስኬታማነት ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባርን በማክበር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

ምክር ቤቱ በባህር ዳርና አካባቢዋ ለሚገኙ ጋዜጠኞች የምርጫ የስነ-ምግባር መመሪያዎችን በተመለከተ ስልጠና ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሞላልኝ መለሰ ለኢዜአ እንደገለጹት መገናኛ ብዙሃን ለምርጫ ፍትሃዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የጎላ ሚና አላቸው።

በኢትዮጵያ ቀጣይ የሚካሄደው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በመጥቀስ፤“የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን አክብረው ሊሰሩ የግድ ይላል”ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውን መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ምርጫውን ለመዘገብ የሚያስችል መመሪያ ጋዜጠኞች መመሪያውንና ኢዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን መሰረተ ባደረገ መልኩ ያለ አድልዎ ሊዘግቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

''ጋዜጠኛ ብሄር የለውም'' ያሉት አቶ ሞላልኝ፤ ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይወግን ወገንተኝነቱን ከእውነት ጋር ብቻ ሊያደርግ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ሳያከብር በሚሰራ ጋዜጠኛና መገናኛ ብዙሃን ላይ ምርጫ ቦርድ የሚወስደው እርምጃ እንዳለ ሆኖ ምክር ቤቱ በግልግል ዳኝነት በሚቀርቡ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔ ይሰጣል ነው ያሉት።

በምርጫ ወቅት የአገርን ሰላም ሊረብሽ በሚችል መልኩ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን የሚያግዝ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኢሌክቶሪያል ሲስተም ተቋም የህግ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ግርማ ናቸው።

ጋዜጠኞች ሁሌም ዘገባዎችን ሲያከናውኑ ህግንና ሙያዊ ስነ-ምግባርን ጠብቀው መሆን እንዳለበት ቢታመንም በተለይ ምርጫ ላይ ልዩ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ያሉት ደግሞ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የሚያግዝ የኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኢሌክቶሪያል ሲስተም ተቋም የህግ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ግርማ ናቸው።

ብሄርን ከብሔር፣ ፓርቲን ከፓርቲ ሊያቃቅሩ ከሚችሉ ዘገባዎች በመቆጠብ ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲአዊነት ሙያዊ ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ጋዜጠኞች ህግን መሰረት በማድረግ ምርጫው ሰላማዊና ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሚሰሩ ተዋናዮች መካከል መሆናቸውን አውቀው ሙያዊና ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፀሃፊ አቶ አቻምየለህ ካሣ በበኩላቸው ምርጫው ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጋዜጠኞች የጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባር ሊረብሹ ከሚችሉ እሳቤዎች እራሳቸውን በማራቅ መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የተሰጠው ስልጠና የበለጠ ለመጠንቀቅ ያግዛል ብለዋል።

''ጋዜጠኝነት በእያንዳንዱ እርምጃ በሙያዊ ስነ-ምግባር መሰረት የሚተገበር ነው'' ያለው ደግሞ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ይኼነው ዋጋቸው ነው።

የጋዜጠኝነት ሙያ ሁሌም ከእውነት ጎን የሚቆም ቢሆንም በምርጫ ወቅት ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

“ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መመስረት አይነተኛ መንገድ በመሆኑ ጋዜጠኛው ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ማሰብና መስራት ይጠበቅበታል” ብሏል።

የምርጫውን ሂደት ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ሃላፊነት በተሞላበት ህግና ደንብ እንዲሁም የተቋሙን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሰረት ባደረገ መልኩ ለመዘገብ መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

በምክርቤቱ አዘጋጅነት በባህር ዳር ከተማ የምርጫ ዘገባ ስነ ምግባር ላይ በተሰጠው ስልጠና ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የመጡ ጋዜጠኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም